ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 2:32-46 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

32. አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ኢዮአብ በሁለቱ ሰዎች ላይ አደጋ ጥሎ በሰይፍ ገድሎአቸዋልና ስላፈ ሰሰው ደም እግዚአብሔር ይበቀለዋል። የእስራኤል ሰራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔርና የይሁዳ ሰራዊት አዛዥ የዬቴሩ ልጅ አሜሳይ ሁለቱም ከእርሱ የተሻሉና ይበልጥ ትክክለኛ ሰዎች ነበሩ።

33. የደማቸውም ዕዳ ለዘላለም በኢዮአብና በዘሩ ራስ ላይ ይሁን። ነገር ግን በዳዊትና በዘሩ፣ በቤቱና በዙፋኑ ላይ የእግዚአብሔር ሰላም ለዘላለም ጸንቶ ይኑር።”

34. ስለዚህም የዮዳሄ ልጅ በናያስ ወጣ፤ ኢዮአብንም መቶ ገደለው፤ እርሱም በምድረ በዳ ባለው በገዛ ምድሩ ተቀበረ።

35. ንጉሡም በኢዮአብ ቦታ የዮዳሄን ልጅ በናያስን በሰራዊቱ ላይ ሾመ፤ በአብያታርም ቦታ ካህኑን ሳዶቅን ተካ።

36. ከዚያም ንጉሡ ሳሚን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “በኢየሩሳሌም ቤት ሠርተህ እዚያው ተቀመጥ፤ ከዚያ ግን የትም እንዳትሄድ፤

37. ነገር ግን ከዚያ ወጥተህ የቄድሮንን ሸለቆ ከተሻገርህ እንደምትሞት ዕወቅ፤ ደምህም በራስህ ላይ ይሆናል።”

38. ሳሚም መልሶ ንጉሡን፣ “መልካም፤ ባሪያህ ጌታዬ ንጉሡ ያለውን ይፈጽማል” አለው፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ብዙ ጊዜ ተቀመጠ።

39. ከሦስት ዓመት በኋላ ግን፣ ከሳሚ አገልጋዮች ሁለቱ ወደ ጌት ንጉሥ፣ ወደ መዓካ ልጅ ወደ አንኩስ ኰበለሉ፤ ለሳሚም፣ “እነሆ፣ አገልጋዮችህ በጌት ናቸው” ተብሎ ተነገረው።

40. ሳሚ ይህን ሲሰማም አህዮቹን ጭኖ አገልጋዮቹን ለመፈለግ ጌት ወዳለው ወደ አንኩስ ሄደ፤ አገልጋዮቹንም ከጌት መልሶ አመጣቸው።

41. ሳሚ ከኢየሩሳሌም ወደ ጌት ሄዶ መመለሱን ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፣

42. ንጉሡ ሳሚን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ ‘ወደ ሌላ ቦታ የሄድህ ዕለት እንደምትሞት ዕወቅ’ ብዬ በእግዚአብሔር ስም አስምዬ አስጠንቅቄህ አልነበረምን? በዚያን ጊዜ አንተም፣ ‘መልካም ነው፤ እኔም እታዘዛለሁ’ ብለኸኝ ነበር፤

43. ታዲያ ለእግዚአብሔር የማልኸውን መሐላ ያልጠበቅኸውና እኔም የሰጠሁህን ትእዛዝ ያልፈጸምኸው ለምንድን ነው?”

44. ንጉሡም መልሶ ሳሚን እንዲህ አለው፤ “በአባቴ በዳዊት ላይ ያደረግህበትን ክፉ ነገር ሁሉ ልብህ ያውቀዋል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ክፉ ሥራህ ብድሩን ይከፍልሃል።

45. ንጉሥ ሰሎሞን ግን ይባረካል፤ የዳዊትም ዙፋን በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”

46. ከዚያም ንጉሡ የዮዳሄን ልጅ በናያስን አዘዘው፤ በናያስም ወጣ፤ ሳሚንም መቶ ገደለው።በዚህ ጊዜም መንግሥቱ በሰሎሞን እጅ ጸና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 2