ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 18:6-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ስለዚህ የሚሄዱበትን ምድር ተከፋፈሉ፤ አክዓብ በአንድ በኩል፣ አብድዩም በሌላ በኩል ሄደ።

7. አብድዩ በመንገድ ላይ ሳለም ኤልያስን አገኘው። አብድዩም ዐወቀው፤ ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ በመንሣት፣ “ጌታዬ ኤልያስ ሆይ፤ በእርግጥ አንተ ነህን?” አለው።

8. እርሱም፣ “አዎን እኔ ነኝ፤ ሂድና ለጌታህ፣ ‘ኤልያስ እዚሁ አለልህ’ ብለህ ንገረው” ሲል መለሰለት።

9. አብድዩም እንዲህ አለው፤ “ምነው ምን አጠፋሁና ነው ባሪያህ እንዲሞት ለአክዓብ አሳልፈህ የምትሰጠው?

10. አምላክህን ሕያው እግዚአብሔርን! ጌታዬ አንተን ለመፈለግ መልእክተኛ ያላከበት ሕዝብና መንግሥት የለም፤ የትኛውም ሕዝብ ሆነ መንግሥት አንተ በዚያ አለመኖርህን ባስታወቀው ጊዜ ሁሉ አንተን አለማግኘቱን ለማረጋገጥ ያስምለው ነበር።

11. አሁን ግን አንተ ወደ ጌታዬ ሄጄ፣ ‘ኤልያስ እዚህ አለልህ’ እንድለው ትፈልጋለህ፤

12. ተለይቼህ ስሄድ የእግዚአብሔር መንፈስ የት እንደሚወስድህ አላውቅም፤ ታዲያ ሄጄ ለአክዓብ ከነገርሁት በኋላ ሳያገኝህ ቢቀር እኔን ይገድለኛል፤ ነገር ግን እኔ ባሪያህ ከጐልማሳነቴ ጀምሮ እግዚአብሔርን አመልካለሁ።

13. ጌታዬ ሆይ፤ ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት ባስገደለች ጊዜ ምን እንዳደረግሁ አልሰማህምን? መቶውን የእግዚአብሔር ነቢያት ወስጄ አምሳ አምሳውን በሁለት ዋሻ በመሸሸግ እህልና ውሃ ሰጠኋቸው።

14. ታዲያ አንተ ሄጄ ለጌታዬ፤ ‘ኤልያስ እዚህ አለልህ’ እንድለው ትፈልጋለህ፤ እርሱም ይገድለኛል!”

15. ኤልያስም፣ “በፊቱ የቆምሁት ሁሉን የሚገዛ ጌታ እግዚአብሔርን፣ ዛሬ በአክዓብ ፊት በርግጥ እገለጣለሁ” አለ።

16. ስለዚህ አብድዩ ሄዶ ይህንኑ ለአክዓብ ነገረው፤ አክዓብም ኤልያስን ለማግኘት ሄደ።

17. ኤልያስንም ባየው ጊዜ፤ “እስራኤልን የምታውክ አንተ ነህን?” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 18