ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 18:36-46 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

36. የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበትም ጊዜ ኤልያስ ወደ መሠዊያው ቀረብ ብሎ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአብርሃም፣ የይስሐቅና የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የእስራኤል አምላክ መሆንህ፣ እኔም የአንተ አገልጋይ መሆኔና ይህን ሁሉ በትእዛዝህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይታወቅ።

37. ይህ ሕዝብ፣ አንተ አምላክ እግዚአብሔር እውነተኛ መሆንህንና ልባቸውን የመለስኸው አንተ መሆንህን ያውቁ ዘንድ እባክህ ስማኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ መልስልኝ።”

38. ከዚያም የእግዚአብሔር እሳት ወርዳ መሥዋዕቱን፣ ዕንጨቱን፣ ድንጋዩንና ዐፈሩን ፈጽማ በላች፤ በጒድጓዱ ውስጥ ያለውንም ውሃ ላሰች።

39. ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያዩ፣ በግንባራቸው ተደፍተው፣ “አምላክ እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ ነው! እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው!” አሉ።

40. ከዚያም ኤልያስ፣ “የበአልን ነቢያት ያዟቸው! አንድም ሰው እንዳያመልጥ” ሲል አዘዘ፤ ሕዝቡም ያዟቸው፤ ኤልያስም ወደ ቂሶን ወንዝ አውርዶ አሳረዳቸው።

41. ኤልያስም አክዓብን፣ “የከባድ ዝናብ ድምፅ ይሰማልና ሂድና ብላ፤ ጠጣም” አለው።

42. ስለዚህ አክዓብ ሊበላና ሊጠጣ ሄደ፤ ኤልያስ ግን ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ጫፍ ወጣ፤ ፊቱንም በጒልበቶቹ መካከል አድርጎ ወደ መሬት አቀረቀረ።

43. አገልጋዩንም፣ “ውጣና ወደ ባሕሩ ተመልከት” አለው።አገልጋዩም ሄዶ ተመለከተና፤ “በዚያ ምንም የለም” አለው።ኤልያስ ሰባት ጊዜ፣ “እንደ ገና ሂድ” አለው።

44. በሰባተኛው ጊዜ አገልጋዩ፣ “እነሆ፤ የሰው እጅ የምታህል ትንሽ ደመና ከባሕሩ እየወጣች ነው” አለው።ኤልያስም፣ “ሂድና አክዓብን፣ ‘ዝናቡ ሳያግድህ፣ ሠረገላህን ጭነህ ውረድ’ ብለህ ንገረው” አለው።

45. ወዲያውኑም ሰማዩ በጥቊር ደመና ተሸፈነ፤ ነፋሱ ነፈሰ፤ ከባድ ዝናብ ጣለ፤ አክዓብም በሠረገላ ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ።

46. የእግዚአብሔርም ኀይል በኤልያስ ላይ ወረደ፤ ኤልያስም ልብሱን ከፍ አድርጎ በቀበቶው ካጠበቀ በኋላ እስከ ኢይዝራኤል ድረስ አክዓብን ቀድሞት ሮጠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 18