ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 18:10-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. አምላክህን ሕያው እግዚአብሔርን! ጌታዬ አንተን ለመፈለግ መልእክተኛ ያላከበት ሕዝብና መንግሥት የለም፤ የትኛውም ሕዝብ ሆነ መንግሥት አንተ በዚያ አለመኖርህን ባስታወቀው ጊዜ ሁሉ አንተን አለማግኘቱን ለማረጋገጥ ያስምለው ነበር።

11. አሁን ግን አንተ ወደ ጌታዬ ሄጄ፣ ‘ኤልያስ እዚህ አለልህ’ እንድለው ትፈልጋለህ፤

12. ተለይቼህ ስሄድ የእግዚአብሔር መንፈስ የት እንደሚወስድህ አላውቅም፤ ታዲያ ሄጄ ለአክዓብ ከነገርሁት በኋላ ሳያገኝህ ቢቀር እኔን ይገድለኛል፤ ነገር ግን እኔ ባሪያህ ከጐልማሳነቴ ጀምሮ እግዚአብሔርን አመልካለሁ።

13. ጌታዬ ሆይ፤ ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት ባስገደለች ጊዜ ምን እንዳደረግሁ አልሰማህምን? መቶውን የእግዚአብሔር ነቢያት ወስጄ አምሳ አምሳውን በሁለት ዋሻ በመሸሸግ እህልና ውሃ ሰጠኋቸው።

14. ታዲያ አንተ ሄጄ ለጌታዬ፤ ‘ኤልያስ እዚህ አለልህ’ እንድለው ትፈልጋለህ፤ እርሱም ይገድለኛል!”

15. ኤልያስም፣ “በፊቱ የቆምሁት ሁሉን የሚገዛ ጌታ እግዚአብሔርን፣ ዛሬ በአክዓብ ፊት በርግጥ እገለጣለሁ” አለ።

16. ስለዚህ አብድዩ ሄዶ ይህንኑ ለአክዓብ ነገረው፤ አክዓብም ኤልያስን ለማግኘት ሄደ።

17. ኤልያስንም ባየው ጊዜ፤ “እስራኤልን የምታውክ አንተ ነህን?” አለው።

18. ኤልያስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “አንተና የአባትህ ቤት እንጂ እኔ እስራኤልን አላወክሁም። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተዋችሁ፣ እነ በኣልንም ተከተላችሁ።

19. አሁንም ሕዝቡ በቀርሜሎስ ተራራ እንዲገናኘኝ ለመላው እስራኤል ጥሪ አድርግ። ከኤልዛቤል ማእድ የሚቀለቡትን አራት መቶ አምሳውን የበኣል ነቢያት፣ አራት መቶውንም የአሼራ ነቢያት አምጣቸው።”

20. ስለዚህ አክዓብ በመላው እስራኤል ጥሪ አደረገ፣ ነቢያቱንም በቀርሜሎስ ተራራ ሰበሰበ።

21. ኤልያስም በሕዝቡ ፊት ቀርቦ፣ “በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉት እስከ መቼ ድረስ ነው? እግዚአብሔር አምላክ ከሆነ እግዚአብሔርን ተከተሉ፤ በኣል አምላክ ከሆነም በኣልን ተከተሉ” አለ።ሕዝቡ ግን አንዲት ቃል አልመለሱም።

22. ከዚያም ኤልያስ እንዲህ አላቸው፤ “ከእግዚአብሔር ነቢያት የተረፍሁ እኔ ብቻ ነኝ፤ በኣል ግን አራት መቶ አምሳ ነቢያት አሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 18