ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 18:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከብዙ ጊዜ በኋላም በሦስተኛው ዓመት እንዲህ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ለኤልያስ መጣለት፤ “ሄደህ ለአክዓብ ተገለጥ፤ እኔም በምድሪቱ ላይ ዝናብ አዘንባለሁ።”

2. ስለዚህም ኤልያስ ራሱን በአክዓብ ፊት ለመግለጥ ሄደ።በዚህ ጊዜ ራብ በሰማርያ ክፋኛ ጸንቶ ነበር።

3. አክዓብም የቤተ መንግሥቱን አዛዥ አብድዩን ጠራው፤ አብድዩም እግዚአብሔርን በጣም የሚፈራ ሰው ነበር።

4. ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት እያስገደለች በነበረበት ጊዜ፣ አብድዩ መቶውን ነቢያት ወስዶ አምሳ አምሳውን በሁለት ዋሻ ውስጥ ሸሽጎ እንጀራና ውሃ ይሰጣቸው ነበር።

5. አክዓብም አብድዩን፣ “ተነሣና በአገሪቱ ውስጥ ወዳሉት ምንጮችና ሸለቆዎች ሂድ፤ ፈረሶቻችንና በቅሎዎቻችን እንዳይሞቱ በሕይወት እንዲቈዩ ምናልባት ሣር እናገኝ ይሆናል።” አለው።

6. ስለዚህ የሚሄዱበትን ምድር ተከፋፈሉ፤ አክዓብ በአንድ በኩል፣ አብድዩም በሌላ በኩል ሄደ።

7. አብድዩ በመንገድ ላይ ሳለም ኤልያስን አገኘው። አብድዩም ዐወቀው፤ ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ በመንሣት፣ “ጌታዬ ኤልያስ ሆይ፤ በእርግጥ አንተ ነህን?” አለው።

8. እርሱም፣ “አዎን እኔ ነኝ፤ ሂድና ለጌታህ፣ ‘ኤልያስ እዚሁ አለልህ’ ብለህ ንገረው” ሲል መለሰለት።

9. አብድዩም እንዲህ አለው፤ “ምነው ምን አጠፋሁና ነው ባሪያህ እንዲሞት ለአክዓብ አሳልፈህ የምትሰጠው?

10. አምላክህን ሕያው እግዚአብሔርን! ጌታዬ አንተን ለመፈለግ መልእክተኛ ያላከበት ሕዝብና መንግሥት የለም፤ የትኛውም ሕዝብ ሆነ መንግሥት አንተ በዚያ አለመኖርህን ባስታወቀው ጊዜ ሁሉ አንተን አለማግኘቱን ለማረጋገጥ ያስምለው ነበር።

11. አሁን ግን አንተ ወደ ጌታዬ ሄጄ፣ ‘ኤልያስ እዚህ አለልህ’ እንድለው ትፈልጋለህ፤

12. ተለይቼህ ስሄድ የእግዚአብሔር መንፈስ የት እንደሚወስድህ አላውቅም፤ ታዲያ ሄጄ ለአክዓብ ከነገርሁት በኋላ ሳያገኝህ ቢቀር እኔን ይገድለኛል፤ ነገር ግን እኔ ባሪያህ ከጐልማሳነቴ ጀምሮ እግዚአብሔርን አመልካለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 18