ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 16:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል በባኦስ ላይ እንዲህ ሲል ወደ አናኒ ልጅ ወደ ኢዩ መጣ፤

2. “ከትቢያ አንሥቼ፣ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግሁህ፤ አንተ ግን በኢዮርብዓም መንገድ ሄድህ፤ ሕዝቤ እስራኤል ኀጢአት እንዲሠራ፣ በኀጢአቱም ለቊጣ እንዲያነሣሣኝ አሳሳትኸው።

3. ስለዚህ ባኦስንና ቤቱን ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ ቤትህንም እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት አደርገዋለሁ።

4. በከተማዪቱ ውስጥ የሚሞቱትን የባኦስን ወገኖች ሁሉ ውሾች ይበሏቸዋል፤ በገጠር የሚሞቱትንም ሁሉ የሰማይ አሞሮች ይቀራመቷቸዋል።”

5. በባኦስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው፣ ሌላው ያደረገው ሥራው በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

6. ባኦስ፣ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቴርሳም ተቀበረ። ልጁም ኤላ በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

7. ከዚህም በቀር የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ ኢዩ አማካይነት በባኦስና በቤቱ ላይ የመጣበት ምክንያት፣ በእጁ ሥራ ያስቈጣው ዘንድ እንደ ኢዮርብዓም ቤት ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራን ሁሉ በማድረጉና ኢዮርብዓምን በማጥፋቱም ጭምር ነው።

8. የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ስድስተኛው ዓመት የባኦስ ልጅ ኤላ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በቴርሳ ተቀምጦም ሁለት ዓመት ገዛ።

9. ከሹማምቱ አንዱና የግማሽ ሠረገሎቹ አዛዥ የሆነው ዘምሪ ዐምፆ ተነሣበት፤ በዚያን ጊዜ ኤላ በቴርሳ ከተማ የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ በሆነው በአርጻ ቤት ጠጥቶ ሰክሮ ነበር፤

10. ዘምሪም ገብቶ ኤላን ገደለው፤ እርሱም በኤላ እግር ተተክቶ፣ የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ነገሠ።

11. ዘምሪ ወዲያው እንደ ነገሠና በዙፋን እንደ ተቀመጠ፣ የባኦስን ቤተ ሰብ በሙሉ ገደለ፤ የሥጋ ዘመድም ሆነ ወዳጅ አንድም ወንድ አላስቀረም።

12. በዚህ ሁኔታም በነቢዩ በኢዩ አማካይነት በባኦስ ላይ በተነገረው በእግዚአብሔር ቃል መሠረት፣ የባኦስን ቤተ ሰብ ሁሉ ፈጀ።

13. ይህም የሆነው ባኦስና ልጁ ኤላ፣ በማይረቡ ጣዖቶቻቸው ምክንያት የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ በሠሩት ኀጢአት ሁሉና፣ እስራኤልም እንዲሠሩ በማድረጉ ነበር።

14. ሌላው ኤላ በዘመኑ የፈጸመውና ያደረገው ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

15. የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ በቴርሳ ሆኖ ሰባት ቀን ብቻ ገዛ። በዚህ ጊዜ ሰራዊቱ የፍልስጥኤማውያን ከተማ የሆነችውን ገባቶንን ከቦ ሰፍሮ ነበር።

16. በዚያም ሰፈር የነበሩ እስራኤላውያን ዘምሪ ዐምፆ ንጉሡን መግደሉን እንደ ሰሙ፣ የሰራዊቱን አዛዥ ዖምሪን በዚያኑ ዕለት እዚያው ሰፈር ውስጥ በእስራኤል ላይ ማንገሣቸውን ዐወጁ።

17. ከዚያም ዖምሪና አብረውት ያሉት እስራኤላውያን ሁሉ ከገባቶን ወደ ላይ ወጥተው ቴርሳን ከበቡ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 16