ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 16:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል በባኦስ ላይ እንዲህ ሲል ወደ አናኒ ልጅ ወደ ኢዩ መጣ፤

2. “ከትቢያ አንሥቼ፣ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግሁህ፤ አንተ ግን በኢዮርብዓም መንገድ ሄድህ፤ ሕዝቤ እስራኤል ኀጢአት እንዲሠራ፣ በኀጢአቱም ለቊጣ እንዲያነሣሣኝ አሳሳትኸው።

3. ስለዚህ ባኦስንና ቤቱን ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ ቤትህንም እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት አደርገዋለሁ።

4. በከተማዪቱ ውስጥ የሚሞቱትን የባኦስን ወገኖች ሁሉ ውሾች ይበሏቸዋል፤ በገጠር የሚሞቱትንም ሁሉ የሰማይ አሞሮች ይቀራመቷቸዋል።”

5. በባኦስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው፣ ሌላው ያደረገው ሥራው በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

6. ባኦስ፣ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቴርሳም ተቀበረ። ልጁም ኤላ በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

7. ከዚህም በቀር የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ ኢዩ አማካይነት በባኦስና በቤቱ ላይ የመጣበት ምክንያት፣ በእጁ ሥራ ያስቈጣው ዘንድ እንደ ኢዮርብዓም ቤት ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራን ሁሉ በማድረጉና ኢዮርብዓምን በማጥፋቱም ጭምር ነው።

8. የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ስድስተኛው ዓመት የባኦስ ልጅ ኤላ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በቴርሳ ተቀምጦም ሁለት ዓመት ገዛ።

9. ከሹማምቱ አንዱና የግማሽ ሠረገሎቹ አዛዥ የሆነው ዘምሪ ዐምፆ ተነሣበት፤ በዚያን ጊዜ ኤላ በቴርሳ ከተማ የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ በሆነው በአርጻ ቤት ጠጥቶ ሰክሮ ነበር፤

10. ዘምሪም ገብቶ ኤላን ገደለው፤ እርሱም በኤላ እግር ተተክቶ፣ የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ነገሠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 16