ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 14:15-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. እግዚአብሔር እስራኤልን በውሃ ውስጥ እንደሚንቀጠቀጥ ሸንበቆ ያንቀጠቅጠዋል፤ የአሼራን ምስል ዐምድ በመሥራት እግዚአብሔርን ለቊጣ ያነሣሡት ስለ ሆነ፣ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻቸው ከሰጣቸው ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እስራኤልን ይነቅላቸዋል፤ ከወንዙም ማዶ ይበትናቸዋል።

16. ኢዮርብዓም ኀጢአት ሠርቶ፣ እስራኤልንም እንዲሠሩ በማድረጉ፣ እግዚአብሔር እስራኤልን ይተዋቸዋል።

17. የኢዮርብዓም ሚስትም ተነሥታ ወደ ቴርሳ ሄደች፤ የቤቱን መድረክ ወዲያው እንደ ተራመደች ልጁ ሞተ፤

18. ከዚያም ቀበሩት፤ እግዚአብሔር በባሪያው በአኪያ አማካይነት እንደ ተናገረ፣ እስራኤል ሁሉ አለቀሱለት።

19. የቀረው የኢዮርብዓም ታሪክ፣ ያደረገው ጦርነትና አገዛዙም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎአል።

20. እርሱም ሃያ ሁለት ዓመት ነግሦ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁ ናዳብም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

21. የሰሎሞን ልጅ ሮብዓም በይሁዳ ነገሠ፤ በነገሠም ጊዜ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመት ነበር፤ እርሱም እግዚአብሔር ለስሙ መጠሪያ እንድትሆን ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጣት በኢየሩሳሌም ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ። እናቱ ናዕማ የተባለች አሞናዊት ነበረች።

22. ይሁዳ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ከአባቶቻቸው ይልቅ እነርሱ በሠሩት ኀጢአት ይበልጥ የቅናት ቊጣውን አነሣሡ፤

23. እንዲሁም በእያንዳንዱ ኰረብታና በየትልልቁ ዛፍ ጥላ ሥር የማምለኪያ ኰረብቶችን አዕማደ ጣዖታት፣ የአሼራን ምስል ዐምድ ለራሳቸው አቆሙ።

24. ከዚያም ይልቅ፣ የቤተ ጣዖት ወንደቃዎች በምድሪቱ ላይ ነበሩ፤ እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት አሳዶ ያስወጣቸው አሕዛብ የፈጸሙትን አስጸያፊ ድርጊት ሁሉ እነዚህም ፈጸሙ።

25. ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ጣለ፤

26. የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የቤተ መንግሥቱን ሀብት ወሰደ፤ ሰሎሞን ያሠራቸው የወርቅ ጋሻዎች እንኳን ሳይቀሩ ሁሉንም ነገር አጋዘ።

27. ስለዚህ ንጉሥ ሮብዓም እነዚህን ለመተካት ሲል፣ የናስ ጋሻዎች አሠርቶ የቤተ መንግሥቱን በር የሚጠብቁት ዘበኞች አዛዦች እንዲይዙ አደረገ።

28. ንጉሡ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚሄድበት ጊዜ ሁሉ፣ ዘቦቹ ጋሻዎቹን ያነግባሉ፤ ከዚያም በዘብ ጥበቃው ክፍል መልሰው ያስቀምጡ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 14