ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 14:10-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. “ ‘ስለዚህ እኔም በኢዮርብዓም ቤት ላይ ጥፋትን አመጣለሁ፤ ባሪያም ይሁን ነጻ ዜጋ የኢዮርብዓምን ወንድ ልጅ ሁሉ ከእስራኤል አስወግዳለሁ፤ ኩበትም ዐመድ እስኪሆን ድረስ እንደሚቃጠል፣ እኔም የኢዮርብዓምን ቤት እንዲሁ አቃጥላለሁ።

11. ከኢዮርብዓም ወገን በከተማ የሞተውን ውሾች፣ በባላገር የሞተውን ደግሞ የሰማይ አሞሮች ይበሉታል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና!’

12. “እንግዲህ አንቺም ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ የምትኖሪበትን ከተማ እግርሽ እንደ ረገጠ፣ ልጁ ይሞታል፤

13. እስራኤልም ሁሉ አልቅሰው ይቀብሩታል። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ከኢዮርብዓም ቤት ሁሉ መልካም ነገር ያገኘበት እርሱ ብቻ ስለ ሆነ፣ በወግ በማዕረግ የሚቀበር እርሱ ብቻ ነው።

14. “ከዚህም በላይ፣ እግዚአብሔር የኢዮርብዓምን ቤተ ሰብ የሚያስወግድ ንጉሥ በእስራኤል ላይ ለራሱ ያስነሣል፤ ይህም ዛሬ፣ አሁኑኑ ይሆናል።

15. እግዚአብሔር እስራኤልን በውሃ ውስጥ እንደሚንቀጠቀጥ ሸንበቆ ያንቀጠቅጠዋል፤ የአሼራን ምስል ዐምድ በመሥራት እግዚአብሔርን ለቊጣ ያነሣሡት ስለ ሆነ፣ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻቸው ከሰጣቸው ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እስራኤልን ይነቅላቸዋል፤ ከወንዙም ማዶ ይበትናቸዋል።

16. ኢዮርብዓም ኀጢአት ሠርቶ፣ እስራኤልንም እንዲሠሩ በማድረጉ፣ እግዚአብሔር እስራኤልን ይተዋቸዋል።

17. የኢዮርብዓም ሚስትም ተነሥታ ወደ ቴርሳ ሄደች፤ የቤቱን መድረክ ወዲያው እንደ ተራመደች ልጁ ሞተ፤

18. ከዚያም ቀበሩት፤ እግዚአብሔር በባሪያው በአኪያ አማካይነት እንደ ተናገረ፣ እስራኤል ሁሉ አለቀሱለት።

19. የቀረው የኢዮርብዓም ታሪክ፣ ያደረገው ጦርነትና አገዛዙም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎአል።

20. እርሱም ሃያ ሁለት ዓመት ነግሦ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁ ናዳብም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

21. የሰሎሞን ልጅ ሮብዓም በይሁዳ ነገሠ፤ በነገሠም ጊዜ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመት ነበር፤ እርሱም እግዚአብሔር ለስሙ መጠሪያ እንድትሆን ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጣት በኢየሩሳሌም ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ። እናቱ ናዕማ የተባለች አሞናዊት ነበረች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 14