ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 14:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዚያን ጊዜ የኢዮርብዓም ልጅ አብያ ታመመ፤

2. ኢዮርብዓም ሚስቱን እንዲህ አላት፤ “ተነሺ፣ የኢዮርብዓም ሚስት መሆንሽ እንዳይታወቅብሽ ሆነሽ፣ ወደ ሴሎ ሂጂ፤ በዚህ ሕዝብ ላይ እንደምነግሥ የነገረኝ ነቢይ አኪያ እነሆ፤ በዚያ ይገኛል።

3. ስትሄጂም ዐሥር እንጀራ፣ ጥቂት ሙልሙል ዳቦ እና አንድ እንስራ ማር ይዘሽ ሂጂ፤ እርሱም በልጁ ላይ የሚደርሰውን ይነግርሻል።”

4. ስለዚህ የኢዮርብዓም ሚስት ያላትን አድርጋ በሴሎ ወደሚገኘው ወደ አኪያ ቤት ሄደች።በዚህ ጊዜ አኪያ ከማርጀቱ የተነሣ ዐይኖቹ ፈዘው ነበር።

5. እግዚአብሔር ግን ለአኪያ፣ “እነሆ፤ የኢዮርብዓም ሚስት ስለ ታመመው ልጇ ልትጠይቅህ ሌላ ሴት መስላ ትመጣለችና እንዲህ ብለህ መልሳት” ብሎ ነገረው።

6. አኪያም የእግሯን ኮቴ ድምፅ እበሩ ላይ እንደ ሰማ እንዲህ አላት፤ “የኢዮርብዓም ሚስት ሆይ ግቢ፤ ግን ለምንድን ነው ሌላ ሴት መስለሽ ለመታየት የፈለግሽው? ለአንቺ ከባድ ነገር እንድነግርሽ ተልኬአለሁ።

7. አሁንም ሂጂና ኢዮርብዓምን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው ብለሽ ንገሪው፤ ‘ከሕዝቡ መካከል አንሥቼ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግሁህ፤

8. ከዳዊት ቤት መንግሥቱን ቀድጄ ለአንተ ሰጠሁህ፤ አንተ ግን በፊቴ መልካም ነገር በማድረግ ብቻ ትእዛዜን እንደ ጠበቀው፣ በፍጹም ልቡም እንደ ተከተለኝ እንደ ባሪያዬ እንደ ዳዊት አልሆንህም።

9. ከአንተ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ አንተ የከፋ ሥራ ሠራህ፤ ለራስህም ከቀለጠ ብረት ሌሎች አማልክትን ሠራህ፤ ቊጣዬን አነሣሣህ፤ ወደ ኋላህም ጣልኸኝ።

10. “ ‘ስለዚህ እኔም በኢዮርብዓም ቤት ላይ ጥፋትን አመጣለሁ፤ ባሪያም ይሁን ነጻ ዜጋ የኢዮርብዓምን ወንድ ልጅ ሁሉ ከእስራኤል አስወግዳለሁ፤ ኩበትም ዐመድ እስኪሆን ድረስ እንደሚቃጠል፣ እኔም የኢዮርብዓምን ቤት እንዲሁ አቃጥላለሁ።

11. ከኢዮርብዓም ወገን በከተማ የሞተውን ውሾች፣ በባላገር የሞተውን ደግሞ የሰማይ አሞሮች ይበሉታል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና!’

12. “እንግዲህ አንቺም ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ የምትኖሪበትን ከተማ እግርሽ እንደ ረገጠ፣ ልጁ ይሞታል፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 14