ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 12:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እስራኤላውያን ሁሉ ሊያነግሡት ወደ ሴኬም ስለ ሄዱ፣ ሮብዓም ወደዚያው ሄደ።

2. የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ከንጉሥ ሰሎሞን ሸሽቶ ከሚኖርበት ከግብፅ ተመልሶ መጣ።

3. ስለዚህም ወደ ኢዮርብዓም ላኩበት፤ እርሱና መላው የእስራኤል ጉባኤም ወደ ሮብዓም መጥተው፣

4. “አባትህ ከባድ ቀንበር ጫነብን፤ አንተ ግን አሁን የአባትህን የጭካኔ አገዛዝ የጫነብንንም ከባድ ቀንበር ብታቀልልን እንገዛልሃለን” አሉት።

5. ሮብዓምም፣ “እንግዲያውስ ሂዱ፤ ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሳችሁ ወደ እኔ ኑ” አላቸው። ስለዚህ ሕዝቡ ሄዱ።

6. ከዚያም ሮብዓም አባቱ ሰሎሞን በሕይወቱ ሳለ ካገለገሉት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ፤ “ለዚህ ሕዝብ ምን መልስ እንድሰጥ ትመክሩኛላችሁ?” አላቸው።

7. እነርሱም፣ “ዛሬ አንተ ለዚህ ሕዝብ አገልጋይ ብትሆን፣ ብትገዛለትና ደስ የሚያሰኝ መልስ ብትሰጠው፣ ምንጊዜም የአንተ አገልጋይ ይሆናል” ብለው መለሱለት።

8. ሮብዓም ግን ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ንቆ፣ አብሮ አደግ የሆኑትንና እርሱን የሚያገለግሉትን ወጣቶች፣

9. “ሐሳብ ለማግኘት፣ የእናንተስ ምክር ምንድን ነው? ‘አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልልን’ ለሚሉኝ ለእነዚህ ሰዎች ምን መልስ እንስጥ?” ሲል ጠየቃቸው።

10. ወጣት አብሮ አደጎቹም፣ እንዲህ አሉት፣ “ ‘አባትህ ከባድ ቀንበር ጫነብን፣ አንተ ግን ቀንበራችንን አቅልልልን’ ላሉህ ለእነዚህ ሰዎች፣ ‘ትንሿ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ይልቅ ትወፍራለች፤

11. አባቴ ከባድ ቀንበር ጫነባችሁ፤ እኔ ግን ከዚያ ይብስ አከብደዋለሁ፤ አባቴ በዐለንጋ ገረፋችሁ፤ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ’ በላቸው!” አሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 12