ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 10:9-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. በአንተ ደስ ተሰኝቶ በእስራኤል ዙፋን ላይ ያስቀመጠህ እግዚአብሔር አምላክህ የተመሰገነ ይሁን፤ እግዚአብሔር በዘላለም ፍቅሩም እስራኤልን ከመውደዱ የተነሣ፣ ፍትሕና ጽድቅ እንዲሰፍን አንተን ንጉሥ አድርጎ አስነሣህ።”

10. ለንጉሡም መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ፣ እጅግ ብዙ ሽቶና የከበረ ድንጋይ ሰጠችው፤ ንግሥተ ሳባ ለንጉሥ ሰሎሞን ያበረከተችለትን ያን ያህል ብዛት ያለው ሽቶ ከዚያ በኋላ ከቶ አልመጣም።

11. ከኦፊር ወርቅ ያመጡት የኪራም መርከቦች፣ እጅግ ብዙ የሰንደል ዕንጨትና የከበሩ ዕንቆችም አመጡ።

12. ንጉሡም የሰንደሉን ዕንጨት ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ለቤተ መንግሥቱ መደገፊያ፣ ለበገናና ለመሰንቆ መሥሪያ አዋለው። ይህን ያህል ብዛት ያለው የሰንደል ዕንጨት እስከ ዛሬ ድረስ ከቶ አልመጣም፤ አልታየምም።

13. ንጉሥ ሰሎሞንም ለንግሥተ ሳባ ከቤተ መንግሥቱ በልግስና ከሚሰጣት ሌላ፣ የፈለገችውንና የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣት፤ ከዚያም ከአጃቢዎቿ ጋር ወደ አገሯ ተመለሰች።

14. ለሰሎሞን በየዓመቱ የሚገባለት ስድስት መቶ ሥልሳ ስድስት መክሊት ወርቅ ነበር።

15. ይህም ከንግድና ከሌላ ገቢ ላይ የሚከፈለውን ቀረጥ፣ የዐረብ ነገሥታት ሁሉ የሚያገቡትንና አገረ ገዦች የሚሰበስቡትን ግብር ሳይጨምር ነው።

16. ንጉሥ ሰሎሞን ከተጠፈጠፈ ወርቅ ሁለት መቶ ታላላቅ ጋሻ አሠራ፤ በእያንዳንዱም ጋሻ የገባው ሦስት መቶ ሰቅል ወርቅ ነበር።

17. እንዲሁም ከተጠፈጠፈ ወርቅ ሦስት መቶ ትንንሽ ጋሻ አሠራ፤ በእያንዳንዱ ጋሻ የገባው ደግሞ ሦስት ምናን ወርቅ ነው። ንጉሡም እነዚህን የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤተ መንግሥት አኖረ።

18. ከዚያም ንጉሡ ከዝሆን ጥርስ ትልቅ ዙፋን አሠርቶ በንጹሕ ወርቅ አስለበጠው።

19. ዙፋኑ ባለ ስድስት ደረጃ ነው፤ በስተ ኋላውም ዐናቱ ላይ ክብ ቅርጽ ሲኖረው፣ ግራና ቀኙ ባለመደገፊያ ነው፤ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመዋል።

20. በስድስቱም ደረጃ ጫፍ ላይ ግራና ቀኝ ስድስት ስድስት አንበሶች ቆመዋል። ይህን የመሰለም ዙፋን በየትኛውም አገር መንግሥት ከቶ ተሠርቶ አያውቅም።

21. ንጉሥ ሰሎሞን የሚጠጣበት ዋንጫ ሁሉ የወርቅ ሲሆን፣ የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበረው ዕቃ በሙሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠራ ነበር፤ በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ብር ይህን ያህል ዋጋ ስላልነበረው፣ ከብር የተሠራ ዕቃ ፈጽሞ አልነበረም።

22. ንጉሡ ከኪራም መርከቦች ጋር አብረው በባሕር ላይ የሚጓዙ የተርሴስ የንግድ መርከቦች ነበሩት። እነዚህም በየሦስት ዓመቱ አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብርና የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣዎችና ዝንጀሮዎች ያመጡ ነበር።

23. ንጉሥ ሰሎሞንም በሀብትና በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ ነበር።

24. ዓለሙ ሁሉ እግዚአብሔር በሰሎሞን ልብ ያኖረውን ጥበብ ለመስማት ወደ እርሱ መምጣት ይፈልግ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 10