ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 1:6-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. አባቱም፣ “ለምን እንዲህ ታደርጋለህ?” ብሎ ገሥጾት አያውቅም ነበር፤ አዶንያስም እጅግ መልከ መልካምና የአቤሴሎም ታናሽ ወንድም ነበር።

7. አዶንያስ ከጽሩያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ ከአብያታር ጋር ተመካከረ፤ እነርሱም ድጋፋቸውን ሰጡት።

8. ነገር ግን ካህኑ ሳዶቅ፣ የዮዳሄ ልጅ በናያስ፣ ነቢዩ ናታን፣ ሳሚ፣ ሬሲና የዳዊት የክብር ዘበኞች ከአዶንያስ ጋር አልተባበሩም።

9. ከዚያም አዶንያስ በዓይንሮጌል አቅራቢያ ባለው የዞሔልት ድንጋይ አጠገብ በጎችን፣ በሬዎችንና የሰቡ ጥጆችን ሠዋ፤ ወንድሞቹን ሁሉ፣ የንጉሡን ልጆች እንዲሁም የቤተ መንግሥቱ ሹማምት የነበሩትን የይሁዳ ሰዎች ሁሉ ጠራ፤

10. ይሁን እንጂ ነቢዩ ናታንንም ሆነ በናያስን፣ የክብር ዘበኞቹንም ሆነ ወንድሙን ሰሎሞንን አልጠራም።

11. ከዚያም ናታን የሰሎሞንን እናት ቤርሳቤህን እንዲህ አላት፤ “ጌታችን ዳዊት ሳያውቅ የአጊት ልጅ አዶንያስ መንገሡን አልሰማሽምን?

12. አሁንም የራስሽንና የልጅሽን የሰሎሞንን ሕይወት እንዴት ማዳን እንደምትችዪ ልምከርሽ፤

13. ወደ ንጉሥ ዳዊት ሂጂና፣ ‘ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ ቀጥሎ ይነግሣል፤ በዙፋኔም ይቀመጣል’ ብለህ ‘ለእኔ ለአገልጋይህ አልማልህልኝም ነበር? ታዲያ አዶንያስ የነገሠው ስለምንድን ነው?’ በዪው፤

14. አንቺ እዚያው ሆነሽ ይህን በምትነግሪው ጊዜ እኔ እገባና ያልሽው ትክክል መሆኑን አረጋግጣለሁ።”

15. ስለዚህ ቤርሳቤህ፣ ሱነማዊቷ አቢሳ በምታገለግልበት ክፍል እርጅና የተጫጫነውን ንጉሥ ለማነጋገር ሄደች።

16. ቤርሳቤህም ለጥ ብላ እጅ ከነሣች በኋላ እፊቱ በጒልበቷ ተንበረከከች።ንጉሡም፣ “ምን ትፈልጊያለሽ?” ሲል ጠየቃት።

17. እርሷም እንዲህ አለችው፣ “ጌታዬ ሆይ፤ ‘ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ ቀጥሎ ይነግሣል፤ በዙፋኔም ይቀመጣል’ ብለህ አንተው ራስህ ለአገልጋይህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ምለህልኝ ነበር።

18. እነሆ፤ አሁንም አዶንያስ ነግሦአል፤ ንጉሥ ጌታዬ አንተ ግን ስለዚህ ነገር አታውቅም።

19. እርሱ በሬዎችን፣ ኮርማዎችንና በጎችን በብዛት ሠውቶአል፤ የንጉሡን ልጆች በሙሉ፣ ካህኑን አብያታርንና የሰራዊቱን አዛዥ ኢዮአብን ጠርቶአል፤ አገልጋይህን ሰሎሞንን ግን አልጠራውም።

20. ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ ከአንተ ቀጥሎ በጌታዬ በንጉሡ ዙፋን ላይ ማን መቀመጥ እንዳለበት እንድታሳውቀው የእስራኤል ዐይን ሁሉ አንተን ይመለከታል።

21. ያለበለዚያ ግን ንጉሥ ጌታዬ ከአባቶቹ ጋር በሚያንቀላፋበት ጊዜ እኔና ልጄ ሰሎሞን እንደ ወንጀለኞች እንቈጠራለን።”

22. እርሷ ከንጉሡ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለች ነቢዩ ናታን ገባ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 1