ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 1:41-49 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

41. አዶንያስና የተጠሩት እንግዶች ሁሉ ግብዣውን በማገባደድ ላይ ሳሉ፣ ይህንኑ ሰሙ፤ ኢዮአብም የመለከቱን ድምፅ ሲሰማ፣ “ይህ በከተማዪቱ ውስጥ የሚሰማው ድምፅ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።

42. ኢዮአብ ገና ተናግሮ ሳይጨርስ፣ የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን ደረሰ፤ አዶንያስም፣ “እንዳንተ ያለ ታማኝ ሰው መልካም ዜና ሳይዝ አይመጣምና ግባ” አለው።

43. ዮናታንም እንዲህ ሲል መለሰ፣ “ነገሩ ከቶ እንዲህ አይደለም! ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን አንግሦታል።

44. ንጉሡ ካህኑ ሳዶቅ፣ ነቢዩ ናታን፣ የዮዳሄ ልጅ በናያስ፣ ከሊታውያንና ፈሊታውያን አብረውት እንዲሄዱ አድርጎአል፤ እነርሱም በንጉሡ በቅሎ አስቀመጡት።

45. ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በግዮን ቀብተው አንግሠውታል። ከዚያም ደስ ብሎአቸው ወጥተዋል፤ ከተማዪቱም ይህንኑ አስተጋብታለች፤ እንግዲህ የሰማችሁት ድምፅ ይኸው ነው።

46. ከዚህም ሌላ ሰሎሞን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦአል።

47. የመንግሥቱ ሹማምትም ወደ ጌታችን ወደ ንጉሥ ዳዊት መጥተው፣ ‘አምላክህ የሰሎሞንን ስም ከአንተ ስም የላቀ፣ ዙፋኑንም ከአንተ ዙፋን የበለጠ ያድርገው’ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸውለታል። ንጉሡም ዐልጋው ላይ ሆኖ በመስገድ፣

48. ‘ዛሬ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጠውን ወራሽ ዐይኔ እንዲያይ የፈቀደ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፣ ምስጋና ይድረሰው’ አለ።”

49. በዚህም አዶንያስና የጠራቸው እንግዶች በሙሉ ደንግጠው ተነሡ፤ በየአቅጣጫውም ተበታተኑ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 1