ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 1:32-43 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

32. ንጉሥ ዳዊትም፣ “ካህኑን ሳዶቅን፣ ነቢዩን ናታንንና የዮዳሄን ልጅ በናያስን ጥሩልኝ” አለ። እነርሱም ንጉሡ ፊት በቀረቡ ጊዜ፣

33. እንዲህ አላቸው፤ “የጌታችሁን አገልጋዮች ይዛችሁ በመሄድ ልጄን ሰሎሞንን በራሴ በቅሎ ላይ አስቀምጡት፤ ወደ ግዮንም ይዛችሁት ውረዱ።

34. በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን ቀብተው በእስራኤል ላይ ያንግሡት፤ ቀንደ መለከት ነፍታችሁም፣ ‘ንጉሥ ሰሎሞን ለዘላለም ይኑር!’ ብላችሁ ጩኹ።

35. አጅባችሁት ወደ ላይ ውጡ፤ ከዚያም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ፤ በእኔም ምትክ ይግዛ፤ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ ሾሜዋለሁ።”

36. የዮዳሄ ልጅ በናያስም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አሜን! የጌታዬ የንጉሡ አምላክ እግዚአብሔር ይህንኑ ያጽናው።

37. እግዚአብሔር ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር እንደ ነበረ ሁሉ፣ ከሰሎሞንም ጋር ይሁን፤ ዙፋኑንም ከጌታዬ ከንጉሥ ዳዊት ዙፋን የበለጠ ያድርገው።”

38. ስለዚህ ካህኑ ሳዶቅ፣ ነቢዩ ናታን፣ የዮዳሄ ልጅ በናያስ፣ ከሊታውያንና ፈሊታውያን ወርደው ሰሎሞንን በንጉሥ ዳዊት በቅሎ አስቀምጠው በማጀብ ወደ ግዮን አመጡት።

39. ካህኑ ሳዶቅም የዘይቱን ቀንድ ከመገናኛው ድንኳን ወስዶ ሰሎሞንን ቀባው፤ ከዚያም ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ ሕዝቡም በሙሉ፣ “ንጉሥ ሰሎሞን ለዘላለም ይኑር!” በማለት ዳር እስከ ዳር አስተጋቡ።

40. ሕዝቡ ሁሉ እንቢልታ እየነፋና እጅግ እየተደሰተ አጀበው፤ ከድምፁ የተነሣም ምድሪቱ ተናወጠች።

41. አዶንያስና የተጠሩት እንግዶች ሁሉ ግብዣውን በማገባደድ ላይ ሳሉ፣ ይህንኑ ሰሙ፤ ኢዮአብም የመለከቱን ድምፅ ሲሰማ፣ “ይህ በከተማዪቱ ውስጥ የሚሰማው ድምፅ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።

42. ኢዮአብ ገና ተናግሮ ሳይጨርስ፣ የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን ደረሰ፤ አዶንያስም፣ “እንዳንተ ያለ ታማኝ ሰው መልካም ዜና ሳይዝ አይመጣምና ግባ” አለው።

43. ዮናታንም እንዲህ ሲል መለሰ፣ “ነገሩ ከቶ እንዲህ አይደለም! ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን አንግሦታል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 1