ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 9:6-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. አገልጋዩ ግን፣ “እነሆ፤ በዚህች ከተማ አንድ የእግዚአብሔር ሰው አለ፤ እርሱም በጣም የተከበረ ነው፤ የሚናገረውም ሁሉ በትክክል ይፈጸማል፤ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን ይነግረን ይሆናልና ወደዚያ እንሂድ” ሲል መለሰለት።

7. ሳኦልም አገልጋዩን፣ “መሄዱን እንሂድ፤ ነገር ግን ለሰውየው ምን እንሰጠዋለን? በስልቻዎቻችን የያዝነው ስንቅ አልቆአል። ለእግዚአብሔር ሰው የምናበረክተውም ስጦታ የለንም፤ ታዲያ ምን አለን?” አለው።

8. አገልጋዩ፣ “እኔ የአንድ ሰቅል ጥሬ ብር ሩብ አለኝ፤ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን ይነግረን ዘንድ ገንዘቡን ለእግዚአብሔር ሰው እሰጠዋለሁ” ሲል በድጋሚ መለሰለት።

9. ቀደም ሲል በእስራኤል ዘንድ አንድ ሰው እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሲሄድ፣ “ኑ ወደ ባለ ራእዩ እንሂድ” ይል ነበር፤ ዛሬ ነቢይ የሚባለው በዚያ ጊዜ ባለ ራእይ ይባል ነበርና።

10. ሳኦልም፣ “መልካም፤ ና እንሂድ” አለው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ከተማ ሄዱ።

11. በከተማዪቱ መዳረሻ ያለውን ኰረብታ በመውጣት ላይ ሳሉ፣ ውሃ ለመቅዳት የሚወጡ ልጃገረዶችን አግኝተው፣ “ባለ ራእዩ እዚህ ነውን?” ሲሉ ጠየቁ።

12. እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤ “አዎን አለ፤ እነሆ፤ ከፊታችሁ ነው፤ ፈጠን በሉ፤ ሕዝቡ በማምለኪያው ኰረብታ ላይ መሥዋዕት ስለሚያቀርብ፣ ወደ ከተማችን ገና ዛሬ መምጣቱ ነው፤

13. ወደ ከተማዪቱም በገባችሁ ጊዜ፣ ለመብላት ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ከመውጣቱ በፊት ታገኙታላችሁ። መሥዋዕቱን እርሱ መባረክ ስላለበት፣ እርሱ እስኪመጣ ድረስ ሕዝቡ መብላት አይጀምርም፤ ከዚያ በኋላ የተጋበዘው ሕዝብ ይበላል፤ አሁኑኑ ውጡ፤ ወዲያው ታገኙታላችሁ።”

14. እነርሱም ወደ ከተማዪቱ ወጡ፤ ወደ ከተማዪቱም በመግባት ላይ ሳሉ፣ እነሆ፤ ሳሙኤል ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ለመውጣት እነርሱ ወዳሉበት አቅጣጫ መጣ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 9