ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 9:17-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ሳሙኤል ሳኦልን ባየው ጊዜ እግዚአብሔር፣ “ያ የነገርሁህ ሰው እነሆ፤ እርሱም ሕዝቤን ይገዛል” አለው።

18. ሳኦልም በቅጥሩ በር ላይ ወደ ሳሙኤል ቀረብ ብሎ፣ “የባለ ራእዩ ቤት የት እንደሆነ ትነግረኛለህ?” ሲል ጠየቀው።

19. ሳሙኤልም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ባለ ራእዩ እኔ ነኝ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር ስለምትበሉ ከፊቴ ቀድማችሁ ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ውጡ፤ ነገ ጠዋት አሰናብትሃለሁ፤ በልብህ ያለውንም እነግርሃለሁ።

20. ከሦስት ቀን በፊት ስለ ጠፉብህ አህዮች አትጨነቅ፤ ተገኝተዋልና። የእስራኤል ምኞት ሁሉ ያዘነበለው ወደ አንተና ወደ አባትህ ቤተ ሰብ ሁሉ አይደለምን?”

21. ሳኦልም፣ “እኔ ከእስራኤል ነገዶች ውስጥ በጣም አነስተኛ ከሆነው ከብንያም ወገን አይደለሁምን? ጐሣዬስ ከብንያም ነገድ ጐሣዎች ሁሉ የሚያንስ አይደለምን? ታዲያ እንዲህ ያለውን ነገር ስለ ምን ትነግረኛለህ?” ብሎ መለሰለት።

22. ከዚያም ሳሙኤል ሳኦልንና አገልጋዩን ወደ አዳራሹ አመጣ፤ ከተጋበዙትም ሠላሳ ያህል ሰዎች ሁሉ በላይ አስቀመጣቸው።

23. ሳሙኤልም ወጥ ቤቱን፣ “ለይተህ አስቀምጥ ብዬ የሰጠሁህን የሥጋ ብልት አምጣው” አለው።

24. ወጥ ቤቱም የጭኑን ሥጋ እንዳለ አምጥቶ በሳኦል ፊት አስቀመጠው። ሳሙኤልም፣ “ይህ፣ ‘እንግዶችን ጋብዣለሁ’ ካልሁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ተወሰነው ጊዜ ድረስ ለአንተ ተለይቶ የተቀመጠልህ ስለ ሆነ ብላው” አለው። ሳኦልም በዚያች ዕለት ከሳሙኤል ጋር አብሮ በላ።

25. ከማምለኪያው ኰረብታ ወደ ከተማዪቱ ከወረዱ በኋላ ሳሙኤል በቤቱ ሰገነት ላይ ከሳኦል ጋር ተነጋገረ።

26. በማለዳ ተነሡ፤ ሳሙኤል ሳኦልን ከሰገነቱ ላይ ጠርቶ፣ “ላሰናብትህ ስለ ሆነ ተዘጋጅ” አለው። ሳኦልም ተዘጋጅቶ እንዳበቃ፣ ከሳሙኤል ጋር ተያይዘው ወደ ውጭ ወጡ።

27. ወደ ከተማዪቱ ዳርቻ እየወረዱ ሳለ፣ ሳሙኤል ሳኦልን፣ “አገልጋይህ ወደ ፊት ቀድሞን እንዲሄድ ንገረው” አለው፤ አገልጋዩም እንደ ተነገረው አደረገ፤ ከዚህ በኋላ ሳሙኤል፣ “አንተ ግን ከእግዚአብሔር የተላከ መልእክት እነግርህ ዘንድ ለጥቂት ጊዜ እዚህ ቈይ” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 9