ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 28:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዚያን ዘመን ፍልስጥኤማውያን፣ እስራኤልን ለመውጋት ሰራዊታቸውን ሰበሰቡ። አንኩስም ዳዊትን፣ “አንተና ሰዎችህ አብራችሁኝ ለጦርነት መውጣት እንዳለባችሁ ዕወቁ” አለው።

2. ዳዊትም፣ “አገልጋይህ ምን እንደሚያደርግ ያን ጊዜ አንተው ራስህ ታያለህ” አለው።አንኩስም፣ “መልካም፤ በዘመኔ ሁሉ የራሴ የክብር ዘብ አደርግሃለሁ” ሲል መለሰለት።

3. በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ሞቶ ነበር፤ እስራኤላውያንም ሁሉ በገዛ ከተማው በአርማቴም አልቅሰው ቀበሩት። ሳኦል ሙታን ሳቢዎችንና መናፍስት ጠሪዎችን ከምድሪቱ አባሮአቸው ነበር።

4. ፍልስኤማውያን ተሰብስበው በመምጣት በሱነም ሲሰፍሩ፣ ሳኦል ደግሞ እስራኤላውያንን ሁሉ ሰብስቦ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ሰፈረ።

5. ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ባየ ጊዜ ፈራ፤ ልቡም እጅግ ተሸበረ።

6. እርሱም እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔር ግን በሕልምም ሆነ በኡሪም ወይም በነቢያት አልመለሰለትም።

7. ሳኦልም አገልጋዮቹን፣ “እስቲ ሙታን ሳቢ ሴት ፈልጉልኝና ሄጄ ልጠይቃት” አላቸው።እነርሱም፣ “እነሆ፤ ሙታን የምትስብ ሴት በዓይንዶር አለች” አሉት።

8. ስለዚህ ሳኦል ሌላ ልብስ በመልበስ መልኩን ለውጦ ከሁለት ሰዎች ጋር በሌሊት ወደ ሴቲቱ ሄደ። እርሱም፣ “እባክሽ፣ መናፍስትን ጠይቂልኝ፤ የምነግርሽንም ሰው አስነሺልኝ” አላት።

9. ሴትዮዋ ግን፣ “እነሆ፤ ሳኦል ሙታን ሳቢዎችንና መናፍስት ጠሪዎችን ከምድሪቱ እንዴት እንዳጠፋና ያደረገባቸውን ታውቃለህ፤ ታዲያ፣ ታስገድለኝ ዘንድ በሕይወቴ ላይ ወጥመድ የዘረጋኸው ለምንድን ነው?” አለችው።

10. ሳኦልም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! በዚህ ነገር ቅጣት አያገኝሽም” ሲል በእግዚአብሔር ስም ማለላት።

11. ሴትዮዋም፣ “ማንን ላስነሣልህ?” ብላ ጠየቀችው።እርሱም፣ “ሳሙኤልን አስነሺልኝ” አላት።

12. ሴትዮዋም ሳሙኤልን ባየችው ጊዜ በታላቅ ድምፅ ጮኽች፤ ሳኦልንም፣ “አንተ ሳኦል ሆነህ ሳለ፣ ለምን አታለልኸኝ?” አለችው።

13. ንጉሡም፣ “አትፍሪ፤ ለመሆኑ ምን እያየሽ ነው?” አላት።ሴትዮዋም፣ “አንድ መንፈስ ከምድር ሲወጣ አያለሁ” አለችው።

14. እርሱም፣ “መልኩ ምን ይመስላል?” ሲል ጠየቃት።እርሷም፣ “ካባ የለበሰ አንድ ሽማግሌ ሰው እየወጣ ነው” አለችው።ሳኦልም ሴትዮዋ ያየችው ሳሙኤል መሆኑን ዐወቀ፤ በመሬትም ላይ ተደፍቶ እጅ ነሣ።

15. ሳሙኤልም ሳኦልን፣ “አስነሥተህ የምታውከኝ ለምንድ ነው?” አለው።ሳኦልም፣ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ፍልስጥኤማውያን እየወጉኝ ነው፤ እግዚአብሔርም ከእኔ ርቆአል፤ በነቢያትም ሆነ በሕልም አልመለሰልኝም፤ ስለዚህ ምን ማድረግ እንደሚገባኝ እንድትነግረኝ ጠራሁህ” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 28