ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 26:9-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ዳዊት ግን አቢሳን እንዲህ አለው፤ “አትግደለው! እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን አንሥቶ ከበደል ነጻ የሚሆን ማን ነው?

10. ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር ራሱ ይቀሥፈዋል፤ ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል፤ ወይም በጦርነት ይሞታል።

11. እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን ከማንሣት እግዚአብሔር ይጠብቀኝ! ነገር ግን በራስጌው አጠገብ ያለውን ጦርና የውሃ መያዣውን ያዝና እንሂድ።”

12. ስለዚህ ዳዊት በሳኦል ራስጌ አጠገብ የነበረውን ጦርና የውሃውን መያዣ ወሰደ፤ ከዚያም ሄዱ፤ ይህን ያየም ሆነ ያወቀ ወይም የነቃ ማንም አልነበረም። ከእግዚአብሔር ዘንድ ከባድ እንቅልፍ ስለወደቀባቸው ሁሉም ተኝተው ነበርና።

13. ከዚህ በኋላ ዳዊት ወደ ማዶ ተሻግሮ በኰረብታው ጫፍ ላይ ራቅ ብሎ ቆመ፤ በመካከላቸውም ሰፊ ርቀት ነበር።

14. ዳዊት ሰራዊቱንና የኔርን ልጅ አብኔርን፣ “አበኔር ሆይ፣ አትመልስልኝምን?” ሲል ተጣራ።አበኔርም፣ “በንጉሡ ላይ የምትጮኽ አንተ ማነህ?” በማለት መለሰ።

15. ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “አንተ ብርቱ ሰው ነህ? በእስራኤልስ ዘንድ አንተን የሚመስል ማን ነው? እነሆ፤ አንድ ሰው ንጉሡን ጌታህን ለመግደል መጥቶ ነበር፤ ታዲያ አንተ ንጉሥ ጌታህን ያልጠበቅኸው ስለምንድን ነው?

16. ያደረግኸው መልካም አይደለም፤ ሕያው እግዚአብሔርን! አንተና ሰዎችህ ሞት ይገባችኋል፤ እግዚአብሔር የቀባውን ጌታችሁን አልጠበቃችሁምና። እስቲ ተመልከት፤ በራስጌው የነበሩት የንጉሡ ጦርና የውሃ መያዣ የት አሉ?”

17. ሳኦል የዳዊትን ድምፅ ለይቶ ስላወቀ፣ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ ይህ ድምፅህ ነውን?” አለው። ዳዊትም፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ አዎን ድምፄ ነው” ሲል መለሰ፤

18. በመቀጠልም፣ “ጌታዬ አገልጋዩን የሚያሳድደው ስለምንድን ነው? ምን አደረግሁ? ምን በደልስ ፈጸምሁ?

19. አሁንም ንጉሥ ጌታዬ የባሪያውን ቃል ያድምጥ፤ እግዚአብሔር በእኔ ላይ አነሣሥቶህ እንደሆነ፣ ቊርባን ይቀበል፤ ነገር ግን ይህን ያደረጉት ሰዎች ከሆኑ፣ በእግዚአብሔር ፊት የተረገሙ ይሁኑ፤ ‘ሂድ ሌሎችን አማልክት አምልክ’ ብለው በእግዚአብሔር ርስት ድርሻ እንዳይኖረኝ ዛሬ አሳደውኛልና።

20. አንድ ሰው በተራራ ላይ ቆቅ እንደሚያድን የእስራኤልም ንጉሥ ቍንጫ ለመፈለግ ስለ ወጣ፣ ደሜ ከእግዚአብሔር ፊት ርቆ በምድር ላይ እንዲፈስ አታድርግ።”

21. ሳኦልም፣ “በድያለሁ፤ ልጄ ዳዊት ሆይ፤ ተመለስ፤ ዛሬ ነፍሴ በፊትህ ስለ ከበረች፣ ከእንግዲህ ወዲያ አልጐዳህም፤ በእርግጥ የሞኝ ሥራ ሠርቻለሁ፤ እጅግ ሲበዛም ተሳስቻለሁ” አለ።

22. ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “የንጉሥ ጦር እነሆ፤ ከወጣቶችህ አንዱ መጥቶ ይውሰዳት።

23. እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ጽድቁና እንደ ታማኝነቱ ይክፈለው። እኔ ግን ዛሬ እግዚአብሔር አንተን በእጄ አሳልፎ ሰጥቶኝ ሳለ እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አላነሣሁም።

24. እነሆ፤ ዛሬ ሕይወትህ በፊቴ እንደ ከበረች ሁሉ፣ የእኔም ሕይወት በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረች ትሁን፤ ከመከራም ሁሉ ያድነኝ።”

25. ከዚያም ሳኦል ዳዊትን፣ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ የተባረክህ ሁን፤ ታላቅ ነገር ታደርጋለህ፤ በእርግጥም ይከናወንልሃል” አለው።ስለዚህም ዳዊት ወደሚሄድበት ሄደ፤ ሳኦልም ወደ ቤቱ ተመለሰ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 26