ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 26:16-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. ያደረግኸው መልካም አይደለም፤ ሕያው እግዚአብሔርን! አንተና ሰዎችህ ሞት ይገባችኋል፤ እግዚአብሔር የቀባውን ጌታችሁን አልጠበቃችሁምና። እስቲ ተመልከት፤ በራስጌው የነበሩት የንጉሡ ጦርና የውሃ መያዣ የት አሉ?”

17. ሳኦል የዳዊትን ድምፅ ለይቶ ስላወቀ፣ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ ይህ ድምፅህ ነውን?” አለው። ዳዊትም፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ አዎን ድምፄ ነው” ሲል መለሰ፤

18. በመቀጠልም፣ “ጌታዬ አገልጋዩን የሚያሳድደው ስለምንድን ነው? ምን አደረግሁ? ምን በደልስ ፈጸምሁ?

19. አሁንም ንጉሥ ጌታዬ የባሪያውን ቃል ያድምጥ፤ እግዚአብሔር በእኔ ላይ አነሣሥቶህ እንደሆነ፣ ቊርባን ይቀበል፤ ነገር ግን ይህን ያደረጉት ሰዎች ከሆኑ፣ በእግዚአብሔር ፊት የተረገሙ ይሁኑ፤ ‘ሂድ ሌሎችን አማልክት አምልክ’ ብለው በእግዚአብሔር ርስት ድርሻ እንዳይኖረኝ ዛሬ አሳደውኛልና።

20. አንድ ሰው በተራራ ላይ ቆቅ እንደሚያድን የእስራኤልም ንጉሥ ቍንጫ ለመፈለግ ስለ ወጣ፣ ደሜ ከእግዚአብሔር ፊት ርቆ በምድር ላይ እንዲፈስ አታድርግ።”

21. ሳኦልም፣ “በድያለሁ፤ ልጄ ዳዊት ሆይ፤ ተመለስ፤ ዛሬ ነፍሴ በፊትህ ስለ ከበረች፣ ከእንግዲህ ወዲያ አልጐዳህም፤ በእርግጥ የሞኝ ሥራ ሠርቻለሁ፤ እጅግ ሲበዛም ተሳስቻለሁ” አለ።

22. ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “የንጉሥ ጦር እነሆ፤ ከወጣቶችህ አንዱ መጥቶ ይውሰዳት።

23. እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ጽድቁና እንደ ታማኝነቱ ይክፈለው። እኔ ግን ዛሬ እግዚአብሔር አንተን በእጄ አሳልፎ ሰጥቶኝ ሳለ እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አላነሣሁም።

24. እነሆ፤ ዛሬ ሕይወትህ በፊቴ እንደ ከበረች ሁሉ፣ የእኔም ሕይወት በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረች ትሁን፤ ከመከራም ሁሉ ያድነኝ።”

25. ከዚያም ሳኦል ዳዊትን፣ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ የተባረክህ ሁን፤ ታላቅ ነገር ታደርጋለህ፤ በእርግጥም ይከናወንልሃል” አለው።ስለዚህም ዳዊት ወደሚሄድበት ሄደ፤ ሳኦልም ወደ ቤቱ ተመለሰ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 26