ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 25:30-44 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

30. እግዚአብሔር ለጌታዬ በሰጠው ተስፋ መሠረት በጎውን ነገር ሁሉ ባደረገለትና በእስራኤልም ላይ ባነገሠው ጊዜ፣

31. ጌታዬ የምታዝንበት ምክንያት ወይም የኅሊና ጸጸት አይኖርህም፤ በከንቱ ያፈሰስኸውም ደም ሆነ በገዛ እጅህ የተበቀልኸው የለምና። እግዚአብሔር በጎ ነገር ባደረገልህ ጊዜ እኔን አገልጋይህን አስበኝ።”

32. ዳዊትም አቢግያን እንዲህ አላት፤ “ዛሬ እንድታገኚኝ ወደ እኔ የላከሽ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።

33. ደም እንዳላፈስና በገዛ እጄ እንዳልበቀል ዛሬ ስለ ጠበቅሽኝ ስለ በጎ ሐሳብሽ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ።

34. ጒዳት እንዳላደርስብሽ የጠበቀኝ የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! እንዲህ በቶሎ መጥተሽ ባታገኚኝ ኖሮ፣ እስኪነጋ ድረስ ለናባል አንድ ወንድ እንኳ ባልተረፈ ነበር።”

35. ከዚያም ዳዊት ያመጣችለትን ከእጇ ተቀብሎ፣ “በሰላም ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እነሆ፤ ቃልሽን ሰምቻለሁ፤ የጠየቅሽኝንም ተቀብያአለሁ” አላት።

36. አቢግያም ወደ ናባል በተመለሰች ጊዜ፣ እነሆ፤ በቤቱ እንደ ንጉሥ ግብዣ ትልቅ ግብዣ አድርጎ አገኘችው፤ ክፉኛም ሰክሮ ልቡ በደስታ ተሞልቶ ነበር። ስለዚህ እስኪነጋ ድረስ ምንም አልነገረችውም።

37. ነግቶ የወይን ጠጁ ስካር ካለፈለት በኋላ የሆነውን ሁሉ ስትነግረው ልቡ ቀጥ አለ፤ ሰውነቱም እንደ ድንጋይ በድን ሆነ።

38. ዐሥር ቀን ያህል ካለፈ በኋላ፣ እግዚአብሔር ናባልን ቀሠፈው፤ እርሱም ሞተ።

39. ዳዊትም ናባል መሞቱን በሰማ ጊዜ፣ “የናባልን ስድብ የተበቀለልኝና እኔን አገልጋዩን ክፉ ከማድረግ የጠበቀኝ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ናባል የሠራውንም ክፉ ነገር በራሱ ላይ መለሰበት” አለ።ዳዊትም አቢግያ ሚስት ትሆነው ዘንድ በመጠየቅ መልእክት ላከባት።

40. አገልጋዮቹም ወደ ቀርሜሎስ ሄደው አቢግያን፣ “ሚስት ትሆኚው ዘንድ እንድንወስድሽ ዳዊት ወደ አንቺ ልኮናል” አሏት።

41. እርሷም ተነሥታ በግምባሯ በመደፋት እጅ ከነሣች በኋላ፣ “እነሆ፤ እኔ ገረድህ አንተን ለማገልገል፣ የጌታዬንም አገልጋዮች እግር ለማጠብ ዝግጁ ነኝ” አለች።

42. አቢግያም ወዲያውኑ በአህያ ላይ ተቀምጣ አምስት አገልጋዮቿን በማስከተል፣ ከዳዊት መልእክተኞች ጋር ሄደች፤ ለዳዊትም ሚስት ሆነችው።

43. እንዲሁም ዳዊት ኢይዝራኤላዊቷን አኪናሆምን አገባ፣ ሁለቱም ሚስቶቹ ሆኑ።

44. ሳኦል ግን የዳዊት ሚስት የነበረችውን ልጁን ሜልኮልን፣ ለጋሊም ተወላጅ ለሌሳ ልጅ ለፈልጢ ሰጥቶ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 25