ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 20:7-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. እርሱም ‘መልካም ነው’ ካለ፣ አገልጋይህን የሚያሰጋው የለም፤ ከተቈጣ ግን፣ ክፉ ነገር እንዳሰበብኝ ታረጋግ ጣለህ።

8. አንተ ግን፤ ለአገልጋይህ በጎነትን አሳይ፣ ከአገልጋይህ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ገብታችኋልና። እኔ በደለኛ ከሆንሁ፣ አንተው ራስህ ግደለኝ፤ ለምንስ ለአባትህ አሳልፈህ ትሰጠኛለህ!”

9. ዮናታንም፣ “ይህ ከአንተ ይራቅ! አባቴ ክፉ ነገር እንዳሰበብህ ባውቅ ኖሮ እንዴት ሳልነግርህ እቀራለሁ?” አለው።

10. ዳዊትም፣ “አባትህ ክፉ ቃል ቢመልስልህ ማን ይነግረኛል?” ብሎ ጠየቀው።

11. ዮናታን፣ “በል ና፤ ወደ ሜዳ እንውጣ” አለው፤ ተያይዘውም ወጡ።

12. ከዚያም ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ምስክር ይሁንብኝ፤ አባቴን ነገ መርምሬ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በዚህ ሰዓት እልክብሃለሁ፤ ስለ አንተ ያለው አመለካከት በጎ ከሆነም አሳውቅሃለሁ።

13. ነገር ግን አባቴ ክፉ አስቦብህ፣ ይህን ሳላሳውቅህ ብቀርና በሰላም እንድትሄድ ባላደርግ፣ እግዚአብሔር ክፉ ያድርግብኝ፤ ከዚያም የባሰ ያምጣብኝ። እግዚአብሔር ከአባቴ ጋር እንደ ነበር እንደዚሁ ከአንተም ጋር ይሁን።

14. አንተም እኔ በሕይወት እስካለሁ ድረስ እንዳልገደል የእግዚአብሔርን በጎነት አድርግልኝ።

15. እግዚአብሔር የዳዊትን ጠላቶች ሁሉ ከምድረ ገጽ በሚደመስስበት ጊዜ እንኳ የበጎነት ሥራህ ከቤተ ሰቤ በፍጹም አይቋረጥ።”

16. ስለዚህ ዮናታን፣ “የዳዊትን ጠላቶች እግዚአብሔር ይፋረዳቸው” በማለት ከዳዊት ቤት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ።

17. ዮናታን ከፍቅሩ የተነሣ ዳዊት እንደ ገና እንዲምልለት አደረገ፤ ዳዊትን የሚወደውም እንደ ራሱ አድርጎ ነበርና።

18. ከዚያም ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ነገ የወር መባቻ በዓል ነው፤ መቀመጫህ ባዶ ስለሚሆን፣ አለመኖርህ ይታወቃል።

19. ከነገ ወዲያ ምሽት ላይ ይህ ችግር በተፈጠረ ዕለት ወደ ተደበቅህበት ስፍራ ሂድና ኤዜል በተባለው ድንጋይ አጠገብ ቈይ።

20. እኔም በአንድ ዒላማ ላይ እንደሚያነጣጥር ሰው ወደ ድንጋዩ አጠገብ ሦስት ፍላጻ እወረውራለሁ፤

21. ከዚያም፣ ‘ሂድና ፍላጾቹን አምጣቸው’ ብዬ አንድ ልጅ እልካለሁ፤ ልጁንም፣ ‘እነሆ፤ ፍላጾቹ ያሉት፣ ከአንተ ወደዚህ ነው፤ ሄደህ አምጣቸው’ ያልሁት እንደሆነ፣ ሕያው እግዚአብሔርን! ክፉ ነገር አያገኝህም፤ አደጋም የለም፤ ውጣና ና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 20