ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 20:27-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

27. በማግስቱም፣ ወር በገባ በሁለተኛው ቀን የዳዊት መቀመጫ ባዶ ነበር፤ ከዚያም ሳኦል ልጁን ዮናታንን፣ “የእሴይ ልጅ ትናንትናም፣ ዛሬም ግብር ላይ ያልተገኘው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።

28. ዮናታንም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ “ዳዊት ወደ ቤተ ልሔም እንዲሄድ እፈቅድለት ዘንድ አጥብቆ ለመነኝ።

29. እርሱም ‘ቤተ ሰባችን በከተማዪቱ ውስጥ መሥዋዕት ስለሚያደርግ በዚያ እንድገኝ ወንድሜ አዞኛልና ልሂድ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ ወንድሞቼን ለማየት እንድሄድ አሰናብተኝ’ አለኝ። በንጉሡ ግብር ላይ ሳይገኝ የቀረውም በዚህ ምክንያት ነው።”

30. ሳኦል በዮናታን ላይ እጅግ ተቈጣ፤ እንዲህም አለው፤ “አንተ የዚያች ጠማማና ዐመፀኛ ሴት ልጅ! ለአንተው ለራስህ ውርደት፣ ለወላጅ እናትህም ዕፍረት ከሚሆነው ከእሴይ ልጅ ጋር መግጠምህን የማላውቅ መሰለህ?

31. የእሴይ ልጅ በምድር ላይ በሕይወት እስካለ ድረስ አንተም ሆንህ መንግሥትህ አትጸኑም። መሞት ስለሚገባው፣ ሰው ላክና አስመጣልኝ!”

32. ዮናታንም፣ “ለምን ይገደላል? ጥፋቱስ ምንድን ነው?” ሲል አባቱን ጠየቀ።

33. ሳኦልም ዮናታንን ለመግደል ጦሩን ወረወረበት። ስለዚህ ዮናታን፣ አባቱ ዳዊትን ለመግደል ቈርጦ መነሣቱን ዐወቀ።

34. ዮናታንም በታላቅ ቊጣ ከግብሩ ላይ ተነሣ፤ አባቱም ዳዊትን ስላዋረደው ወሩ በገባ በሁለተኛው ቀን ምግብ አልበላም።

35. በማግስቱ ጠዋት ዮናታን አንድ ትንሽ ልጅ አስከትሎ፣ ከዳዊት ጋር ወደ ተቃጠረበት ቦታ ሄደ፤

36. ልጁንም፣ “ሩጥ! የምሰዳቸውን ፍላጻዎች ፈልጋቸው” አለው፤ ልጁም በሮጠ ጊዜ፣ ከእርሱ አሳልፎ አንድ ፍላጻ ወረወረ።

37. ልጁም የዮናታን ፍላጻ ባረፈበት ስፍራ እንደ ደረሰ፤ ዮናታን ጠራውና፣ “ፍላጻው ካንተ ወዲያ ዐልፎ የለምን?” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 20