ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 19:6-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ሳኦልም ዮናታንን ካዳመጠው በኋላ፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም” ብሎ ማለ።

7. ስለዚህም ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ የተባባሉትን ሁሉ ነገረው፤ ወደ ሳኦልም አመጣው፤ ዳዊትም እንደ ቀድሞው በፊቱ ቆመ።

8. እንደ ገና ሌላ ጦርነት ተነሣ፤ ዳዊትም ወጥቶ ፍልስጥኤማውያንን ወጋቸው፤ ከፊቱም እስኪሸሹ ድረስ እጅግ መታቸው።

9. ነገር ግን ሳኦል ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ መጣበት፤ ዳዊት በገናውን ይደረድር ነበር፣

10. ሳኦልም ከግድግዳው ጋር ሊያጣብቀው ጦሩን ወረወረበት፤ ነገር ግን ዳዊት ዘወር በማለቱ ሳኦል የወረወረው ጦር በግድግዳው ላይ ተሰካ። በዚያች ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ።

11. ሳኦልም የዳዊትን ቤት ከበው በማለዳ እንዲገድሉት ሰዎችን ላከ። የዳዊት ሚስት ሜልኮል ግን፣ “ሕይወትህን ለማትረፍ በዚህች ሌሊት ካልሸሸህ፣ በነገው ቀን ትገደላለህ” ብላ አስጠነቀቀችው።

12. ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አሾልካ አወረደችው፣ እርሱም ሸሽቶ አመለጠ።

13. ከዚያም ሜልኮል የጣዖት ምስል ወስዳ በዐልጋው ላይ አጋደመችው፤ በራስጌውም የፍየል ጠጒር አኖረች፤ በልብስም ሸፈነችው።

14. ሳኦል ዳዊትን እንዲይዙት ሰዎች በላከ ጊዜ ሜልኮል፣ “እርሱ ታሞአል” አለቻቸው።

15. ሳኦልም ሰዎቹ ዳዊትን እንዲያዩት መልሶ ላካቸው፤ እርሱም፣ “እገድለው ዘንድ ከነዐልጋው አምጡልኝ” አላቸው።

16. የተላኩትም ሰዎች በገቡ ጊዜ እነሆ፤ የጣዖት ምስሉ በዐልጋው ላይ ተጋድሞ በራስጌውም የፍየል ጠጒር ተደርጎለት ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 19