ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 18:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ዳዊት ከሳኦል ጋር የሚያደርገውን ንግግር እንዳበቃ፤ የዮናታን ነፍስ ከዳዊት ነፍስ ጋር ተቈራኘች፤ እንደራሱም አድርጎ ወደደው።

2. ከዚያች ዕለት አንሥቶ ሳኦል ዳዊትን አብሮት እንዲኖር አደረገ፤ ወደ አባቱም ቤት እንዲመለስ አላሰናበተውም።

3. ዮናታን እንደ ራሱ አድርጎ ስለ ወደደው፣ ከዳዊት ጋር ኪዳን አደረገ፤

4. ዮናታን የለበሰውን ካባ አውልቆ ከነጦር ልብሱ፣ በተጨማሪም ሰይፉን፣ ቀስቱንና መታጠቂያውን ሰጠው።

5. ሳኦል በሚልከው በማናቸውም ስፍራ፣ ዳዊት ተልእኮውን በሚገባ ይፈጽም ስለ ነበር፣ በሰራዊቱ ላይ ሾመው፤ ይህም ሕዝቡን በሙሉ፣ የሳኦልንም የጦር ሹማምት ደስ አሰኘ።

6. ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ከገደለ በኋላ፣ ሰዎቹ ወደየቤታቸው በሚመለሱበት ጊዜ፣ ሴቶች ከበሮና መሰንቆ ይዘው እየዘፈኑ፣ እየጨፈሩና እልል እያሉ ንጉሥ ሳኦልን ለመቀበል ከእስራኤል ከተሞች ሁሉ ወጡ።

7. ሴቶቹም እንዲህ ሲሉ በመቀባበል ዘፈኑ፤“ሳኦል ሺህ ገደለ፤ዳዊት ግን ዐሥር ሺህ ገደለ።”

8. ሳኦል እጅግ ተቈጣ፤ ይህም ነገር አላስደሰተውም። እርሱም፣ “ለዳዊት ዐሥር ሺህ አሉለት፤ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ! እንግዲህ መንግሥት እንጂ ሌላ ምን ቀረው” አለ።

9. ከዚያች ዕለት አንሥቶ ሳኦል ዳዊትን በቅናት ዐይን ይመለከተው ጀመር።

10. በማግስቱም ከእግዚአብሔር የታዘዘ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በኀይል መጣበት፣ በዚህ ጊዜ ዳዊት ወትሮ እንደሚያደርገው ሁሉ በገና ሲደረድር፣ ሳኦል በቤቱ ሆኖ ትንቢት ይናገር ነበር። ሳኦል በእጁ ጦር ይዞ ነበር፤

11. እርሱም፣ “ዳዊትን ከግድግዳው ጋር አጣብቀዋለሁ” ብሎ በማሰብ ጦሩን ወረወረበት፤ ዳዊት ግን ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ።

12. እግዚአብሔር ከእርሱ ተለይቶ ከዳዊት ጋር ስለ ሆነ፣ ሳኦል ዳዊትን ፈራው።

13. ስለዚህ ዳዊትን ከአጠገቡ በማራቅ የሺህ አለቃ አደረገው። ዳዊትም ሰራዊቱን እየመራ በፊታቸው ይወጣና ይገባ ነበር።

14. እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር የሚያደርገው ነገር ሁሉ ይሳካለት ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 18