ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 17:50-58 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

50. በዚህ ሁኔታ ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ብቻ ፍልስጥኤማዊውን አሸነፈው፤ በእጁም ሰይፍ ሳይዝ ፍልስጥኤማዊውን መታው፤ ገደለውም።

51. ዳዊት ሮጦ በላዩ ላይ ቆመ፤ ከዚያም የፍልስጥኤማዊውን ሰይፍ ከሰገባው መዞ አወጣው፤ እርሱንም ከገደለው በኋላ ራሱን በሰይፍ ቈረጠው።ፍልስጥኤማውያንም ጀግናቸው መሞቱን ባዩ ጊዜ ሸሹ።

52. ከዚህ በኋላ የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች ተነሥተው እየፎከሩ ፍልስጥኤማውያንን እስከ ጌት መግቢያና እስከ ዔቅሮን በሮች ድረስ አሳደዷቸው። የፍልስጥኤማውያንም ሬሳ ከሸዓይራይም አንሥቶ እስከ ጌት ከዚያም እስከ ዔቅሮን በሮች ባለው መንገድ ላይ ወድቆ ነበር።

53. እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመለሱ፤ ሰፈራቸውንም በዘበዙ።

54. ዳዊትም የፍልስጥኤማዊውን ራስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ ነገር ግን የፍልስጥኤማዊውን የጦር መሣሪያዎች በራሱ ድንኳን ውስጥ አስቀመጠ።

55. ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ለመግጠም በሚሄድበት ጊዜ ሳኦል ተመልክቶ የሰራዊቱን አዛዥ አበኔርን፣ “አበኔር ሆይ፤ ይህ ልጅ የማን ነው?” ሲል ጠየቀው።አበኔርም፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ አላውቅም” ብሎ መለሰለት።

56. ንጉሡም፣ “እንግዲህ ወጣቱ የማን ልጅ እንደሆነ ተከታትለህ ድረስበት” አለው።

57. ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ እንደ ተመለሰ፣ አበኔር ይዞ ንጉሡ ዘንድ አቀረበው። በዚህ ጊዜ ዳዊት የጎልያድን ራስ በእጁ ይዞ ነበር።

58. ሳኦልም፣ “አንተ ወጣት፣ የማን ልጅ ነህ?” ሲል ጠየቀው።ዳዊትም፣ “እኔ የአገልጋይህ የቤተ ልሔሙ ሰው የእሴይ ልጅ ነኝ” ሲል መለሰ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 17