ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 17:34-44 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

34. ዳዊት ግን ሳኦልን እንዲህ አለው፣ “አገልጋይህ የአባቱን በጎች በሚጠብቅበት ጊዜ፤ አንበሳ ወይም ድብ መጥቶ ከመንጋው አንድ በግ ነጥቆ ሲሄድ፣

35. ተከትዬ በመሄድ እመታውና ከአፉ አስጥል ነበር፤ ፊቱን ወደ እኔ በሚያዞርበትም ጊዜ ጒሮሮውን ይዤ በመምታት እገድለው ነበር።

36. ባሪያህ አንበሳውንም ድቡንም ገድሎአል፤ ይህም ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሰራዊት ተገዳድሮአልና መጨረሻው ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል።

37. ከአንበሳ መዳፍና ከድብ መንጋጋ ያዳነኝ እግዚአብሔር አሁንም ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።”ሳኦልም፣ “ሂድ፤ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሁን” አለው።

38. ከዚያም ሳኦል ለዳዊት የገዛ ራሱን የጦር ልብስ አለበሰው፤ ጥሩር አጠለቀለት፤ ከናስ የተሠራ ቍርም ደፋለት።

39. ዳዊትም ይህን ዐይነት ልብስ ለብሶ ስለማያውቅ፣ ሰይፉን በጦር ልብሱ ላይ ታጥቆ ለመራመድ ሞከረ፤እርሱም ሳኦልን፣ “ያልተለማመድሁት ስለ ሆነ እንደዚህ ሆኜ መራመድ አልችልም” አለው። ስለዚህ ሁሉንም አወለቀው።

40. ከዚያም በትሩን በእጁ ያዘ፤ አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች ከወንዝ መርጦ በእረኛ ኮረጆው ከጨመረ በኋላ፣ ወንጭፉን በእጁ ይዞ፣ ወደ ፍልስጥኤማዊው ቀረበ።

41. ፍልስጥኤማዊውም፣ ጋሻ ጃግሬውን እፊት እፊቱ በማስቀደም፣ ወደ ዳዊት እየቀረበ መጣ።

42. እርሱም ዳዊትን ትኵር ብሎ ሲያየው፣ ደም ግባት ያለው፣ መልከ መልካምና አንድ ፍሬ ልጅ ነበር፤ ስለዚህ ናቀው።

43. ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፣ “በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው፤ በአማልክቱም ስም ረገመው።

44. እርሱም፣ “እስቲ ወደኔ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና፣ ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 17