ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 17:16-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. ፍልስጥኤማዊውም አርባ ቀን ሙሉ ጠዋትና ማታ ፊት ለፊት ብቅ እያለ ቆሞ ይታያቸው ነበር።

17. በዚህ ጊዜ እሴይ ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ይህን ዐሥር ኪሎ የተጠበሰ እሸትና ዐሥር እንጀራ ለወንድሞችህ ይዘህ ወዳሉበት የጦር ሰፈር በቶሎ ድረስ።

18. ይህንም ዐሥር የአይብ ጥፍጥፍ ለክፍል አዛዣቸው አብረህ ውሰድ፤ ወንድሞችህም እንዴት እንደሆኑ አይተህ፣ ደኅንነታቸውን የሚያረጋግጥ ምልክት ከእነርሱ ዘንድ አምጣልኝ።

19. እነርሱ ከሳኦልና ከእስራኤል ሰዎች ሁሉ ጋር ሆነው በዔላ ሸለቆ ከፍልስጥኤማውያን ጋር እየተዋጉ ናቸው።”

20. ዳዊት በማለዳ በጎቹን ለጠባቂ ትቶ፣ እሴይ እንዳዘዘው ዕቃውን ይዞ ጒዞ ጀመረ። ልክ ሰራዊቱ እየፎከረ ለውጊያ ቦታ ቦታውን ለመያዝ በሚወጣበት ጊዜ ከጦሩ ሰፈር ደረሰ።

21. እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን ቦታ ቦታቸውን ይዘው ፊት ለፊት ተፋጠው ይጠባበቁ ነበር።

22. ዳዊት ዕቃውን ከስንቅ ጠባቂው ዘንድ አስቀምጦ ወደ ጦሩ ግንባር ሮጠ፤ ወንድሞቹንም አግኝቶ ደኅንነታቸውን ጠየቀ።

23. ከእነርሱም ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ፣ ከጌት የመጣው ፍልስጥኤማዊው ጀግና ጎልያድ ከሰልፉ መካከል ወጥቶ እንደ ለመደው ሲደነፋ፤ ዳዊት ሰማ።

24. እስራኤላውያንም ሰውየውን ባዩት ጊዜ ሁሉም በታላቅ ፍርሀት ከፊቱ ሸሹ።

25. እስራኤላውያንም እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው በየቀኑ እየመጣ እስራኤልን እንደሚገዳደር ታያላችሁ? ይህን ሰው ለሚገድል፣ ንጉሡ ብዙ ሀብት ይሰጠዋል፤ ሴት ልጁን ይድርለታል፣ የአባቱንም ቤት በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያደርገዋል” ይባባሉ ነበር።

26. ዳዊት በአጠገቡ የቆሙትን ሰዎች፣ “ለመሆኑ ይህን ፍልስጥኤማዊ ገድሎ እንዲህ ያለውን ውርደት ከእስራኤል ለሚያስወግድ ሰው ምን ይደረግለታል? ደግሞስ የሕያው እግዚአብሔርን ሰራዊት ይገዳደር ዘንድ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እርሱ ማነው?” ሲል ጠየቀ።

27. እነርሱም፣ “ለሚገድለው ሰው የሚደረግለትማ ይህ ነው” ሲሉ አስቀድመው ያሉትን ደግመው ነገሩት።

28. ታላቅ ወንድሙ ኤልያብ፣ ዳዊት ከሰዎች ጋር ሲነጋገር በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጥቶ፣ “ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂት በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? ትዕቢትህንና የልብህን ክፋት ዐውቃለሁ፤ የመጣኸው ጦርነቱን ለማየት ብቻ ነው” አለው።

29. ዳዊትም፣ “ታዲያ ምን አደረግሁ? መጠየቅ እንኳ አልችልም?” አለ።

30. ከዚያም ወደ ሌላ ሰው ዘወር ብሎ፣ ያንኑ ጥያቄ ጠየቀ፤ ሰዎቹም እንደ ቀድሞው መለሱለት፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 17