ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 15:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሳሙኤል ሳኦልን እንዲህ አለው፤ “በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ቀብቼ እንዳነግሥህ፣ እግዚአብሔር የላከው እኔን ነው፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር የመጣውን መልእክት አድምጥ።

2. የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ፣ አማሌቃውያን በመንገድ ላይ ስለ ተቃወሙት እቀጣቸዋለሁ።

3. አሁንም ሂድ፤ አማሌቃውያንን ውጋ፤ ያላቸውንም ሁሉ ፈጽመህ አጥፋ፤ አንዱንም አታስቀር፤ ወንዱንና ሴቱን፣ ልጁንና ሕፃኑን፣ የቀንድ ከብቱንና በጉን፣ ግመሉንና አህያውን ግደል።” ’

4. ስለዚህ ሳኦል ሰዎቹን ጥላኢም በተባለ ቦታ ሰብስቦ ቈጠራቸው፤ እነርሱም ሁለት መቶ ሺህ እግረኛ ወታደሮችና ከይሁዳም ዐሥር ሺህ ሰዎች ነበሩ፤

5. ሳኦልም ወደ አማሌቅ ከተማ ሄዶ በአንዲት ሸለቆ ውስጥ አደፈጠ።

6. እርሱም፣ ቄናውያንን፣ “ከእነርሱ ጋር እንዳላጠፋችሁ ከአማሌቃውያን ራቁ፤ ተለዩአቸውም፤ እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር በወጡ ጊዜ፣ ቸርነት አድርጋችሁላቸዋልና” አላቸው። ስለዚህ ቄናውያን ከአማሌቃውያን ተለዩ።

7. ከዚያም ሳኦል አማሌቃውያንን ከኤውላጥ አንሥቶ በምሥራቅ ግብፅ እስካለው እስከ ሱር ድረስ ወጋቸው።

8. የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግን ከነሕይወቱ ማረከው፤ ሕዝቡን ሁሉ በሰይፍ ስለት ፈጽሞ አጠፋቸው።

9. ነገር ግን ሳኦልና ሰራዊቱ አጋግን፣ ምርጥ ምርጡን በግና የቀንድ ከብት፣ የሰባውን ጥጃና ጠቦት፣ መልካም የሆነውን ሁሉ ሳይገድሉ ተውት። እነዚህን ፈጽመው ለማጥፋት ፈቃደኞች አልነበሩም፤ ነገር ግን የተናቀውንና የማይጠቅመውን ሁሉ አጠፉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 15