ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 12:5-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ሳሙኤልም፣ “በእጄ ምንም እንዳላገኛችሁ እግዚአብሔርና እርሱ የቀባው ዛሬ በእናንተ ላይ ምስክሮች ናቸው” አላቸው።እነርሱም፣ “እርሱ ምስክር ነው” አሉ።

6. ከዚያም ሳሙኤል ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “ሙሴንና አሮንን የመረጠ፣ የቀድሞ አባቶቻችሁንም ከግብፅ ያወጣ እግዚአብሔር ነው።

7. አሁንም ለእናንተና ለአባቶቻችሁ እግዚአብሔር ስላደረገው የጽድቅ ሥራ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ስለምሟገታችሁ በዚህ ቁሙ።

8. “ያዕቆብ ወደ ግብፅ ከገባ በኋላ፣ አባቶቻችሁ እግዚአብሔር እንዲረዳቸው ወደ እርሱ ጮኹ፤ እግዚአብሔርም የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብፅ ምድር አውጥተው በዚህ ስፍራ እንዲኖሩ ያደረጉትን ሙሴንና አሮንን ላከላቸው።

9. “እነርሱ ግን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ረሱት፤ ስለዚህ ለሐጾር የጦር አዛዥ ለሲሣራ፣ ለፍልስጥኤማውያንና ለሞዓብ ንጉሥ አሳልፎ ሸጣቸው።

10. እነርሱም፣ ‘ኀጢአት ሠርተናል፤ እግዚአብሔርን ትተን በአሊምንና አስታሮትን አምልከናል። አሁን ግን ከጠላቶቻችን እጅ ታደገን፤ እኛም አንተን እናመልካለን’ ሲሉ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።

11. ከዚያም እግዚአብሔር ይሩበኣልን፣ ባርቅን፣ ዮፍታሔንና ሳሙኤልን ልኮ በሰላም ትኖሩ ዘንድ በዙሪያችሁ ካሉት ጠላቶቻችሁ እጅ ታደጋችሁ።

12. የአሞናውያን ንጉሥ ናዖስ እንደ መጣባችሁ ባያችሁ ጊዜ ግን፣ ምንም እንኳ አምላካችሁ እግዚአብሔር ንጉሣችሁ ቢሆንም፣ ‘አይሆንም፤ የሚገዛን ንጉሥ እንፈልጋለን’ አላችሁ።

13. “አሁንም የጠየቃችሁትና የመረጣችሁት ንጉሥ ይኸው፤ እነሆ፣ እግዚአብሔር በላያችሁ ንጉሥ አንግሦአል።

14. እግዚአብሔርን የምትፈሩና የምታመልኩ፣ የምትታዘዙትና በትእዛዛቱ ላይ የማታምፁ ከሆነ፣ እንዲሁም እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ከተከተላችሁ መልካም ይሆንላችኋል።

15. እግዚአብሔርን የማትታዘዙና በትእዛዛቱም ላይ የምታምፁ ከሆነ ግን፣ እጁ በአባቶቻችሁ ላይ እንደ ነበረች ሁሉ በእናንተም ላይ ትሆናለች።

16. “ስለዚህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር በዐይናችሁ ፊት የሚያደርገውንም ይህን ታላቅ ነገር ተመልከቱ፤

17. አሁን የስንዴ መከር ጊዜ አይደለምን? እኔ ነጐድጓድና ዝናብ እንዲልክ ወደ እግዚአብሔር እጮኻለሁ፤ እናንተም ንጉሥ እንዲነግሥላችሁ በመጠየቃችሁ በእግዚአብሔር ፊት የቱን ያህል የከፋ ድርጊት እንደፈጸማችሁ ያን ጊዜ ታውቃላችሁ።”

18. ከዚህ በኋላ ሳሙኤል ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ በዚያኑ ዕለት እግዚአብሔር ነጐድጓድና ዝናብ ላከ። ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርንና ሳሙኤልን እጅግ ፈሩ።

19. ሕዝቡም ሁሉ ሳሙኤልን፣ “ሌላው በደላችን ሳያንስ፣ ንጉሥ እንዲነግሥልን በመጠየቃችን ተጨማሪ ክፋት ስላደረግን እንዳንሞት፣ ለአገልጋዮችህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን” አሉት።

20. ሳሙኤልም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “አትፍሩ፤ ይህን ሁሉ ክፋት አድርጋችኋል፤ ሆኖም እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ አምልኩት እንጂ እግዚአብሔርን ከመከተል ፈቀቅ አትበሉ።

21. ሊጠቅሟችሁ ወይም ሊያድኗችሁ የማይችሉ ምናምንቴ ነገሮችን አትከተሉ፤ ከንቱ ናቸውና።

22. እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ ያደርጋችሁ ዘንድ ስለ ወደደ፣ ስለ ታላቅ ስሙ ሲል እግዚአብሔር ሕዝቡን አይተውም።

23. ከዚህም በላይ እኔ ለእናንተ ከመጸለይ ወደ ኋላ በማለት እግዚአብሔርን መበደል ከእኔ ይራቅ፤ እኔ መልካምና ቅን የሆነውን መንገድ አስተምራችኋለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 12