ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 12:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሳሙኤል ለመላው እስራኤል እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ ያላችሁኝን ሁሉ ሰምቼ ንጉሥ አንግሼላችኋለሁ።

2. ንጉሥ ሆኖ የሚመራችሁንም ሰው እነሆ፤ አግኝታችኋል። እኔም ዕድሜዬ ገፍቶአል፤ ጠጒሬም ሸብቶአል፤ ልጆቼም አብረዋችሁ አሉ፤ ከወጣትነት ጊዜዬ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ስመራችሁ ቈይቻለሁ።

3. እነሆ፤ ከፊታችሁ ቆሜአለሁ፤ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ፤ የማንን በሬ ወሰድሁ? የማንን አህያ ወሰድሁ? ማንን አታለልሁ? በማንስ ላይ ግፍ ሠራሁ? አይቶ እንዳላየ ለመሆንስ ከማን እጅ ጒቦ ተቀበልሁ? ከእነዚህ ሁሉ አንዱን እንኳ አድርጌ ከሆነ እመልስላችኋለሁ።”

4. እነርሱም፣ “አላታለልኸንም ወይም ግፍ አልሠራህብንም፤ ከማንም እጅ አንዳች ነገር አልተቀበልህም” ብለው መለሱለት።

5. ሳሙኤልም፣ “በእጄ ምንም እንዳላገኛችሁ እግዚአብሔርና እርሱ የቀባው ዛሬ በእናንተ ላይ ምስክሮች ናቸው” አላቸው።እነርሱም፣ “እርሱ ምስክር ነው” አሉ።

6. ከዚያም ሳሙኤል ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “ሙሴንና አሮንን የመረጠ፣ የቀድሞ አባቶቻችሁንም ከግብፅ ያወጣ እግዚአብሔር ነው።

7. አሁንም ለእናንተና ለአባቶቻችሁ እግዚአብሔር ስላደረገው የጽድቅ ሥራ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ስለምሟገታችሁ በዚህ ቁሙ።

8. “ያዕቆብ ወደ ግብፅ ከገባ በኋላ፣ አባቶቻችሁ እግዚአብሔር እንዲረዳቸው ወደ እርሱ ጮኹ፤ እግዚአብሔርም የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብፅ ምድር አውጥተው በዚህ ስፍራ እንዲኖሩ ያደረጉትን ሙሴንና አሮንን ላከላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 12