ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 11:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. አሞናዊው ናዖስ ወጥቶ ኢያቢስ ገለዓድን ከበባት፤ የኢያቢስም ሰዎች ሁሉ፣ “ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርግ፣ እኛም እንገዛልሃለን” አሉት።

2. አሞናዊው ናዖስ፣ “ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን የማደርገው የእያንዳንዳችሁን ቀኝ ዐይን አውጥቼ እስራኤልን ሁሉ ካዋረድሁ በኋላ ብቻ ነው” ሲል መለሰ።

3. የኢያቢስም ሽማግሌዎች፣ “ወደ መላው እስራኤል መልእክተኞችን እንድንልክ የሰባት ቀን ጊዜ ስጠን፤ ሊታደገን የሚመጣ ሰው ከሌለ፣ ለአንተ እንገዛለን” አሉት።

4. መልእክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ መጥተው ይህን ለሕዝቡ በተናገሩ ጊዜ፣ ሕዝቡ ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤

5. በዚህ ጊዜ፣ ሳኦል በሬዎቹን እየነዳ ከዕርሻ ተመለሰ፤ እርሱም፣ “ሕዝቡ የሚያለቅሰው ምን ሆኖ ነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም የኢያቢስ ሰዎች ያሏቸውን ነገሩት።

6. ሳኦል ይህን በሰማ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ወረደበት፤ እጅግ ተቈጣ።

7. ጥንድ በሬዎች ወስዶ ቈራረጠ፤ ሥጋቸውንም በመልእክተኞች እጅ ልኮ፣ “ሳኦልንና ሳሙኤልን የማይከተል ሰው በሬው እንደዚህ ይቈራረጣል” ሲል በመላው እስራኤል አስነገረ። ታላቅ ፍርሀት ከእግዚአብሔር ዘንድ በሕዝቡ ላይ ወደቀ፤ ሕዝቡም እንደ አንድ ሰው ሆኖ ወጣ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 11