ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 10:9-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ሳኦል ከሳሙኤል ተለይቶ ለመሄድ ፊቱን በመለሰ ጊዜ፣ እግዚአብሔር የሳኦልን ልብ ለወጠው፤ ምልክቱም ሁሉ በዚያ ዕለት ተፈጸመ።

10. ጊብዓ በደረሱ ጊዜ የነቢያቱ ጉባኤ አገኙት፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ወረደበት፤ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ተናገረ።

11. ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ከነቢያቱ ጋር ትንቢት ሲናገር ባዩት ጊዜ፣ እርስ በርሳቸው፣ “የቂስን ልጅ ምን ነካው? ሳኦልም ከነቢያት ወገን ነውን?” ሲሉ ተጠያየቁ።

12. በዚያ ነዋሪ የሆነ አንድ ሰው፣ “የእነርሱስ አባት ማን ነው?” ብሎ መለሰ። ስለዚህ፣ “ሳኦልም ከነቢያት ወገን ነውን?” የሚል ምሳሌያዊ አነጋገር ሆነ።

13. ሳኦል ትንቢት መናገሩን ከፈጸመ በኋላ ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ሄደ።

14. በዚህ ጊዜ የሳኦል አጎት እርሱንና አገልጋዩን፣ “የት ነበራችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።እርሱም፣ “አህዮቹን ፍለጋ ሄደን ነበር፤ እንደማይገኙ በተረዳን ጊዜ ግን ወደ ሳሙኤል ሄድን” አለው።

15. የሳኦል አጎትም፣ “እባክህ፣ ሳሙኤል ያለህን ንገረኝ” አለው።

16. ሳኦልም መልሶ፣ “አህዮቹ መገኘታቸውን ገልጦ ነገረን” አለው። ይሁን እንጂ ስለ መንገሡ ሳሙኤል የነገረውን ለአጎቱ አልተናገረም።

17. ሳሙኤል የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ምጽጳ ወደ እግዚአብሔር ፊት ጠርቶ፣

18. እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እስራኤልን ከግብፅ አወጣሁት፤ ከግብፃውያን እጅ ይጨቁኗችሁ ከነበሩት ከሌሎቹ መንግሥታት ሁሉ እጅ ታደግኋችሁ።”

19. ዛሬ ግን ከመከራችሁና ከጭንቃችሁ ሁሉ የሚያድናችሁን አምላካችሁን ንቃችሁ፤ ‘የለም፤ ንጉሥ አንግሥልን’ አላችሁ። ስለዚህ በየነገዳችሁና በየጐሣችሁ ሆናችሁ በእግዚአብሔር ፊት ቅረቡ።”

20. ሳሙኤል የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ ባቀረበ ጊዜ፣ የብንያም ነገድ ተመረጠ።

21. ከዚያም የብንያምን ነገድ በየጐሣው ወደ ፊት አቀረበ፤ የማጥሪ ጐሣም ተመረጠ። በመጨረሻም የቂስ ልጅ ሳኦል ተመረጠ። እርሱ ግን ተፈልጎ አልተገኘም።

22. ሰዎቹም፣ “ሰውየው መጥቶአልን?” ሲሉ እግዚአብሔርን ጠየቁ። እግዚአብሔርም፣ “አዎን፤ ነገር ግን በዕቃ መካከል ተሸሽጎአል” አለ።

23. እነርሱም ሮጠው ከተደበቀበት አመጡት፤ በሕዝቡ መካከል በቆመ ጊዜም ቁመቱ ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ ከትከሻው በላይ ዘለግ ያለ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 10