ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 10:5-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. “ከዚያ በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጦር ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ጊብዓ ትሄዳለህ። ወደ ከተማዪቱ እንደ ደረስህም የነቢያት ጉባኤ በመሰንቆ፣ በከበሮ፣ በእምቢልታና በበገና ታጅበው ትንቢት እየተናገሩ ከማምለኪያው ኰረብታ ላይ ሲወርዱ ታገኛቸዋለህ።

6. የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ይወርድብሃል፤ ከእነርሱ ጋር ትንቢት ትናገራለህ፤ እንደ ሌላ ሰውም ሆነህ ትለወጣለህ።

7. እነዚህ ምልክቶች በተፈጸሙ ጊዜ እጅህ ማድረግ የምትችለውን ሁሉ አድርግ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና።

8. “ከፊቴ ቀድመህ ወደ ጌልገላ ውረድ፤ እኔም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕቱን ለማቅረብ ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ነገር ግን ወደ አንተ መጥቼ ምን ማድረግ እንዳለብህ እስክነግርህ ድረስ ሰባት ቀን መቆየት አለብህ።”

9. ሳኦል ከሳሙኤል ተለይቶ ለመሄድ ፊቱን በመለሰ ጊዜ፣ እግዚአብሔር የሳኦልን ልብ ለወጠው፤ ምልክቱም ሁሉ በዚያ ዕለት ተፈጸመ።

10. ጊብዓ በደረሱ ጊዜ የነቢያቱ ጉባኤ አገኙት፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ወረደበት፤ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ተናገረ።

11. ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ከነቢያቱ ጋር ትንቢት ሲናገር ባዩት ጊዜ፣ እርስ በርሳቸው፣ “የቂስን ልጅ ምን ነካው? ሳኦልም ከነቢያት ወገን ነውን?” ሲሉ ተጠያየቁ።

12. በዚያ ነዋሪ የሆነ አንድ ሰው፣ “የእነርሱስ አባት ማን ነው?” ብሎ መለሰ። ስለዚህ፣ “ሳኦልም ከነቢያት ወገን ነውን?” የሚል ምሳሌያዊ አነጋገር ሆነ።

13. ሳኦል ትንቢት መናገሩን ከፈጸመ በኋላ ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ሄደ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 10