ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 10:19-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. ዛሬ ግን ከመከራችሁና ከጭንቃችሁ ሁሉ የሚያድናችሁን አምላካችሁን ንቃችሁ፤ ‘የለም፤ ንጉሥ አንግሥልን’ አላችሁ። ስለዚህ በየነገዳችሁና በየጐሣችሁ ሆናችሁ በእግዚአብሔር ፊት ቅረቡ።”

20. ሳሙኤል የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ ባቀረበ ጊዜ፣ የብንያም ነገድ ተመረጠ።

21. ከዚያም የብንያምን ነገድ በየጐሣው ወደ ፊት አቀረበ፤ የማጥሪ ጐሣም ተመረጠ። በመጨረሻም የቂስ ልጅ ሳኦል ተመረጠ። እርሱ ግን ተፈልጎ አልተገኘም።

22. ሰዎቹም፣ “ሰውየው መጥቶአልን?” ሲሉ እግዚአብሔርን ጠየቁ። እግዚአብሔርም፣ “አዎን፤ ነገር ግን በዕቃ መካከል ተሸሽጎአል” አለ።

23. እነርሱም ሮጠው ከተደበቀበት አመጡት፤ በሕዝቡ መካከል በቆመ ጊዜም ቁመቱ ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ ከትከሻው በላይ ዘለግ ያለ ነበር።

24. ሳሙኤልም መላውን ሕዝብ፣ “እግዚአብሔር የመረጠውን ሰው አያችሁን? ከሕዝቡ ሁሉ የሚስተካከለው ማንም የለም” አለ።ከዚያም ሕዝቡ፣ “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” ብሎ ጮኸ።

25. ሳሙኤልም ለንጉሥ የሚገባውን ወግና ሥርዐት ለሕዝቡ ገልጦ ካስረዳ በኋላ በመጽሐፍ ጽፎ በእግዚአብሔር ፊት አኖረው። ከዚህ በኋላ ሳሙኤል እያንዳንዱን ሰው ወደየቤቱ አሰናበተ።

26. ሳኦልም ጊብዓ ወዳለው ቤቱ ሄደ፤ እግዚአብሔርም ልባቸውን የነካው ኀያላን ሰዎች አብረውት ሄዱ።

27. አንዳንድ ምናምንቴ ሰዎች ግን፣ “እንዲህ ያለ ሰው እንዴት ሊያድነን ይችላል?” በማለት ናቁት፤ ስጦታም አላመጡለትም። ሳኦል ግን ዝም አለ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 10