ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 10:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚያም ሳሙኤል የዘይቱን ብርሌ ወስዶ፣ ዘይቱን በሳኦል ራስ ላይ ካፈሰሰ በኋላ እንዲህ ሲል ሳመው፤ “በርስቱ ላይ ገዥ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶህ የለምን?

2. ዛሬ ከእኔ ተለይተህ ስትሄድ፣ በብንያም ወሰን ላይ በምትገኘው ጼልጻህ በተባለች ስፍራ በራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ። እነርሱም፣ ‘የምትፈልጋቸው አህዮች ተገኝተዋል፤ አሁን አባትህ ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ፣ “ስለ ልጄ ምን ባደርግ ይሻለኛል?” እያለ በመጨነቅ ላይ ነው’ ይሉሃል።

3. “አንተም ጒዞህን በመቀጠል በታቦር እስካለው እስከ ትልቁ ዛፍ ድረስ ትሄዳለህ፤ እዚያም ሦስት ሰዎች፣ አንዱ ሦስት የፍየል ግልገል፣ ሌላው ሦስት ዳቦ፣ ሌላው ደግሞ የወይን ጠጅ የተሞላበት አቁማዳ ይዘው ወደ እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ሲወጡ ያገኙሃል።

4. እነርሱም ሰላም ይሉሃል፤ ሁለት ዳቦ ይሰጡሃል፤ አንተም ትቀበላቸዋለህ።

5. “ከዚያ በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጦር ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ጊብዓ ትሄዳለህ። ወደ ከተማዪቱ እንደ ደረስህም የነቢያት ጉባኤ በመሰንቆ፣ በከበሮ፣ በእምቢልታና በበገና ታጅበው ትንቢት እየተናገሩ ከማምለኪያው ኰረብታ ላይ ሲወርዱ ታገኛቸዋለህ።

6. የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ይወርድብሃል፤ ከእነርሱ ጋር ትንቢት ትናገራለህ፤ እንደ ሌላ ሰውም ሆነህ ትለወጣለህ።

7. እነዚህ ምልክቶች በተፈጸሙ ጊዜ እጅህ ማድረግ የምትችለውን ሁሉ አድርግ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና።

8. “ከፊቴ ቀድመህ ወደ ጌልገላ ውረድ፤ እኔም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕቱን ለማቅረብ ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ነገር ግን ወደ አንተ መጥቼ ምን ማድረግ እንዳለብህ እስክነግርህ ድረስ ሰባት ቀን መቆየት አለብህ።”

9. ሳኦል ከሳሙኤል ተለይቶ ለመሄድ ፊቱን በመለሰ ጊዜ፣ እግዚአብሔር የሳኦልን ልብ ለወጠው፤ ምልክቱም ሁሉ በዚያ ዕለት ተፈጸመ።

10. ጊብዓ በደረሱ ጊዜ የነቢያቱ ጉባኤ አገኙት፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ወረደበት፤ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ተናገረ።

11. ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ከነቢያቱ ጋር ትንቢት ሲናገር ባዩት ጊዜ፣ እርስ በርሳቸው፣ “የቂስን ልጅ ምን ነካው? ሳኦልም ከነቢያት ወገን ነውን?” ሲሉ ተጠያየቁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 10