ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዮሐንስ 4:12-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. እግዚአብሔርን ያየ ከቶ ማንም የለም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ ግን እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል፤ ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል።

13. መንፈሱን ስለ ሰጠን፣ እኛ በእርሱ እንደምንኖር እርሱም በእኛ እንደሚኖር እናውቃለን።

14. አብ ልጁን የዓለም አዳኝ ይሆን ዘንድ እንደላከው ዐይተናል፤ እንመሰክራለንም።

15. ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምኖ በሚመሰክር ሁሉ፣ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል፤ እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል።

16. ስለዚህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እናውቃለን፤ በፍቅሩም እናምናለን።እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል።

17. በዚህም ዓለም እርሱን እንመስላለንና። በፍርድ ቀን ድፍረት ይኖረን ዘንድ፣ ፍቅር በዚህ ዐይነት በመካከላችን ፍጹም ሆኖአል፤

18. በፍቅር ፍርሀት የለም፤ ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሀትን አውጥቶ ይጥላል፤ ፍርሀት ከቅጣት ጋር የተያያዘ ነውና። የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም።

19. እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን።

20. ማንም፣ “እግዚአብሔርን እወደዋለሁ” እያለ ወንድሙን ቢጠላ፣ እርሱ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን መውደድ አይችልምና።

21. እርሱም “እግዚአብሔርን የሚወድ ሁሉ ወንድሙን መውደድ ይገባዋል” የሚለውን ይህን ትእዛዝ ሰጥቶናል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዮሐንስ 4