ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕንባቆም 3:10-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ተራሮች አዩህ፤ ተጨነቁም፤የውሃ ሞገድ ዐልፎ ሄደ፤ቀላዩ ደነፋ፤ማዕበሉንም ወደ ላይ አነሣ።

11. ከሚወረወሩ ፍላጾችህ፣ከሚያብረቀርቅ የጦርህ ነጸብራቅ የተነሣም፣ፀሓይና ጨረቃ በቦታቸው ቆሙ።

12. በምድር ላይ በመዓት ተመላለስህ፤ሕዝቦችንም በቊጣ ረገጥሃቸው።

13. ሕዝብህን ለመታደግ፣የቀባኸውንም ለማዳን ወጣህ፤የክፋትን ምድር መሪ ቀጠቀጥህ፤ከራስ ጠጒሩ እስከ እግር ጥፍሩም ዕርቃኑን አስቀረኸው። ሴላ

14. እንደ ዐውሎ ነፋስ ሊበታትነን የመጣውን፣ምስኪኑን በስውር በመዋጥ የሚደሰተውን፣የሰራዊት አለቃ ራስ፣በገዛ ጦሩ ወጋህ።

15. ታላላቅ ውሆችን በመናጥ፣ባሕሩን በፈረሶችህ ረገጥህ።

16. እኔ ሰማሁ፤ ልቤም ደነገጠብኝ፤ከንፈሬ ከድምፁ የተነሣ ተንቀጠቀጠ፤ፍርሀት እስከ ዐጥንቴ ዘልቆ ገባ፤እግሬም ተብረከረከ፤ሆኖም በሚወረን ሕዝብ ላይ እስኪመጣ ድረስ፣የጥፋትን ቀን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ።

17. ምንም እንኳ የበለስ ዛፍ ባያፈራ፣ከወይን ተክልም ፍሬ ባይገኝ፣የወይራም ዛፍ ፍሬ ባይሰጥ፣ዕርሻዎችም ሰብል ባይሰጡ፣የበጎች ጒረኖ እንኳ ባዶውን ቢቀር፣ላሞችም በበረት ውስጥ ባይገኙ፣

18. እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤በድነቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።

19. ጌታ እግዚአብሔር ኀይሌ ነው፤እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፤በከፍታዎችም ላይ ያስሄደኛል።ለመዘምራን አለቃ፣ በባለ አውታር መሣሪያዎቼ የተዘመረ መዝሙር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕንባቆም 3