ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 20:9-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ነገር ግን በጊብዓ ላይ የምናደርገው ይህ ነው፤ በዕጣው መሠረት እንዘምትበታለን።

10. ከመላው የእስራኤል ነገዶችም ለሰራዊቱ ስንቅ እንዲይዙ፣ ከመቶው ዐሥር፣ ከሺው አንድ መቶ፣ ከዐሥር ሺው ደግሞ አንድ ሺህ ሰው እንወስዳለን። ከዚያም ሰራዊቱ በብንያም ወደምትገኘው ጊብዓ በሚደርስበት ጊዜ፣ ነዋሪዎችዋ በእስራኤል ላይ ለፈጸሙት አስነዋሪ ድርጊት ተገቢውን ቅጣት ይሰጣቸዋል።”

11. ስለዚህ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው በመተባበር በከተማዪቱ ላይ ዘመቱባት።

12. የእስራኤል ነገዶች ለመላው የብንያም ነገድ እንዲህ በማለት መልእክተኞች ላኩ፣ “በመካከላችሁ የተፈጸመው ይህ ክፉ ድርጊት ምንድ ነው?

13. አሁንም እነርሱን ገድለን ይህን ክፉ ድርጊት ከእስራኤል እንድናስወግድ፣ እነዚያን የጊብዓን ወስላቶች አሳልፋችሁ ስጡን።”ብንያማውያን ግን ወገኖቻቸውን እስራኤላውያንን አልሰሟቸውም ነበር፤

14. ስለዚህ እስራኤላውያንን ለመውጋት ከየከተሞቻቸው በአንድነት ወደ ጊብዓ መጡ።

15. ብንያማውያንም ከመላው የጊብዓ ነዋሪዎች መካከል ከተመረጡት ሰባት መቶ ሰዎች ሌላ፣ ሰይፍ የታጠቁ ሃያ ስድስት ሺህ ሰዎች በአንድ አፍታ ከየከተሞቻቸው በተጨማሪ አሰባሰቡ።

16. በእነዚህም ሁሉ መካከል እያንዳንዳቸው ድንጋይ ወንጭፈው ጠጒር እንኳ የማይስቱ ሰባት መቶ ምርጥ ግራኞች ነበሩ።

17. እስራኤላውያን፣ ብንያማውያንን ሳይጨምር፣ ሰይፍ የታጠቁ አራት መቶ ሺህ ተዋጊዊች አሰባሰቡ።

18. እስራኤላውያን ወደ ቤቴል ወጡ፤ እግዚአብሔርንም፣ “ብንያማውያንን ለመውጋት ከመካከላችን ማን ቀድሞ ይውጣ?” ሲሉ ጠየቁ። እግዚአብሔርም፣ “ይሁዳ ቀድሞ ይውጣ” ብሎ መለሰ።

19. በማግሥቱ ጧት እስራኤላውያን ተነሥተው በጊብዓ አጠገብ ሰፈሩ፤

20. የእስራኤል ሰዎች ብንያማውያንን ለመውጋት ሄዱ፤ በጊብዓ ለሚያደርጉትም ውጊያ ቦታ ቦታቸውን ያዙ።

21. ብንያማውያን ከጊብዓ ወጡ፤ በዚያችም ዕለት ከእስራኤላውያን ሃያ ሁለት ሺህ ሰዎች ገደሉ።

22. ይሁን እንጂ እስራኤላውያን እርስ በርሳቸው ተበረታትተው በመጀመሪያው ቀን ተሰልፈው በነበረበት ስፍራ ላይ እንደ ገና ቦታ ቦታቸውን ያዙ።

23. እስራኤላውያን ወጥተው እስኪመሽ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት አለቀሱ፤ “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን ለመግጠም እንደ ገና እንውጣን?” ብለው እግዚአብሔርን ጠየቁ። እግዚአብሔርም፣ “አዎን፤ ውጡና ግጠሟቸው” ብሎ መለሰላቸው።

24. በሁለተኛው ቀን እስራኤላውያን ወደ ብንያማውያን ተጠጉ።

25. በዚሁ ጊዜም ብንያማውያን፣ እስራኤላውያንን ሊወጉ ከጊብዓ ወጡ፤ እንደ ገናም በሙሉ ሰይፍ የታጠቁ ዐሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች ገደሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 20