ምዕራፎች

 1. 1
 2. 2
 3. 3
 4. 4
 5. 5
 6. 6
 7. 7
 8. 8
 9. 9
 10. 10
 11. 11
 12. 12
 13. 13
 14. 14
 15. 15
 16. 16
 17. 17
 18. 18
 19. 19
 20. 20
 21. 21
 22. 22

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 3 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በሰርዴስ ላለው ቤተ ክርስቲያን

1. “በሰርዴስ ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ ሰባቱን የእግዚአብሔር መናፍስትና ሰባቱን ከዋክብት በእጁ የያዘው እንዲህ ይላል፤ ሥራህን ዐውቃለሁ፤ በስም ሕያው ነህ፤ ነገር ግን ሞተሃል።

2. ስለዚህ ንቃ፤ ሊሞት የተቃረበውን የቀረውን ነገር አጽና፤ ሥራህ በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትም።

3. እንግዲህ የተቀበልኸውንና የሰማኸውን አስታውስ፤ ታዘዘውም፤ ንስሓም ግባ። ባትነቃ ግን እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ፤ በየትኛው ሰዓት እንደምመጣብህም አታውቅም።

4. ነገር ግን ልብሳቸውን ያላሳደፉ ጥቂት ሰዎች በሰርዴስ ከአንተ ጋር አሉ፤ እነርሱም ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ፤ ይህ የሚገባቸው ነውና።

5. ድል የሚነሣም እንደ እነርሱ ነጭ ልብስ ይለብሳል፤ እኔም በአባቴና በመላእክቱ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም።

6. መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።

በፊላድልፍያ ላለው ቤተ ክርስቲያን

7. “በፊላድልፍያ ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው፣ የዳዊትንም መክፈቻ በእጁ የያዘው እንዲህ ይላል፤ እርሱ የከፈተውን ማንም ሊዘጋው አይችልም፤ የዘጋውንም ማንም ሊከፍተው አይችልም።

8. ሥራህን ዐውቃለሁ፤ እነሆ፤ ማንም ሊዘጋው የማይችል የተከፈተ በር በፊትህ አድርጌአለሁ። ኀይልህ ትንሽ እንደሆነ ዐውቃለሁ፤ ሆኖም ቃሌን ጠብቀሃል፤ ስሜንም አልካድህም።

9. እነሆ፣ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉት፣ የሚዋሹት፣ ከሰይጣን ማኅበር የሆኑት ወደ አንተ እንዲመጡ በእግርህ ሥር እንዲሰግዱ፣ እኔ እንደ ወደድሁህም እንዲያውቁ አደርጋለሁ።

10. በትዕግሥት እንድትጸና የሰጠሁህን ትእዛዜን ስለ ጠበቅህ፣ እኔ ደግሞ በምድር ላይ የሚኖሩትን ሊፈትናቸው በዓለም ሁሉ ላይ ከሚመጣው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ።

11. ቶሎ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጥብቀህ ያዝ።

12. ድል የሚነሣውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ውስጥ ዐምድ አደርገዋለሁ፤ ከዚያም ከቶ አይወጣም። የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም ይኸውም ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን የአዲሲቱን ኢየሩሳሌም ስም በእርሱ ላይ እጽፋለሁ፤ አዲሱን ስሜንም በእርሱ ላይ እጽፋለሁ።

13. መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።

በሎዶቅያ ላለው ቤተ ክርስቲያን

14. “በሎዶቅያ ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ አሜን የሆነው፣ ደግሞም ታማኝና እውነተኛ ምስክር የሆነው፣ የእግዚአብሔርም ፍጥረት ገዥ የሆነው እንዲህ ይላል፤

15. ቀዝቃዛ ወይም ትኵስ እንዳልሆንህ ሥራህን ዐውቃለሁ፤ ቀዝቃዛ ወይም ትኵስ ብትሆን በወደድሁ ነበር።

16. እንግዲህ ለብ ያልህ ብቻ እንጂ ትኵስ ወይም ቀዝቃዛ ስላልሆንህ ከአፌ አውጥቼ ልተፋህ ነው።

17. ‘ሀብታም ነኝ፤ ባለጠጋ ነኝ አንዳችም አያስፈልገኝም’ ትላለህ፤ ነገር ግን ጐስቋላ፣ ምስኪን፣ ድኻ፣ ዕውርና፣ የተራቈትህ መሆንህን አታውቅም።

18. ስለዚህ ሀብታም እንድትሆን፣ በእሳት የነጠረ ወርቅ እንድትገዛ፣ የዕራቍትነትህ ኀፍረት እንዳይታይ፣ ነጭ ልብስ እንድትለብስና ለማየት እንድትችል ዐይንህን በኵል እንድትኳል እመክርሃለሁ።

19. እኔ የምወዳቸውን እገሥጻለሁ፤ እቀጣለሁም። ስለዚህ ትጋ፤ ንስሓም ግባ።

20. እነሆ፤ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ሰምቶ በሩን ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ ገብቼ ከእርሱ ጋር እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።

21. እኔ ድል ነሥቼ ከአባቴ ጋር በእርሱ ዙፋን ላይ እንደ ተቀመጥሁ፣ ድል የሚነሣውንም ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ።

22. መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።