ምዕራፎች

 1. 1
 2. 2
 3. 3
 4. 4
 5. 5
 6. 6
 7. 7
 8. 8
 9. 9
 10. 10
 11. 11
 12. 12
 13. 13
 14. 14
 15. 15
 16. 16
 17. 17
 18. 18
 19. 19
 20. 20
 21. 21
 22. 22
 23. 23
 24. 24
 25. 25

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የሕዝቅያስ መታመም

1. በዚያ ጊዜ ሕዝቅያስ በጠና ታሞ ሊሞት ተቃርቦ ነበር። የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ እርሱ ሄዶ፣ “እግዚአብሔር፣ ‘ትሞታለህ ከእንግዲህ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል’ ብሎሃል” አለው።

2. ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤

3. “እግዚአብሔር ሆይ፤ በታማኝነትና በፍጹም ልብ በፊትህ እንደሄድሁ፣ አንተን ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ አስብ፤” ሕዝቅያስም ምርር ብሎ አለቀሰ።

4. ኢሳይያስ የመካከለኛውን አደባባይ አልፎ ከመሄዱ በፊት የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እርሱ መጣ፤

5. “ተመለስና የሕዝቤን አለቃ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፤ ‘የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፣ እፈውስሃለሁ። ከዛሬ ሦስት ቀን በኋላ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ትወጣለህ፤

6. በዕድሜህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ፤ አንተንና ይህችንም ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ስለ እኔ ስለ ራሴና ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ስል ይህችን ከተማ እከላከልላታለሁ።’ ”

7. ከዚያም ኢሳይያስ፣ “ትኵስ የበለስ ጥፍጥፍ አዘጋጁ” አላቸው፤ እነርሱም አዘጋጅተው ዕባጩ ላይ አደረጉለት፤ ተፈወሰም።

8. ሕዝቅያስም፣ “እግዚአብሔር እኔን ስለ መፈወሱ፣ ከሦስት ቀን በኋላም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስለ መውጣቴ ምልክቱ ምንድን ነው?” ሲል ኢሳይያስን ጠየቀው።

9. ኢሳይያስም፣ “እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም ምልክቱ ይህ ነው፤ ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት ይቅደምን? ወይስ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ?” ሲል ጠየቀው።

10. ሕዝቅያስም መልሶ፣ “ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት መሄዱ ቀላል ነገር ነው፤ ይልቁን ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ” አለ።

11. ከዚያም ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም አካዝ በሠራው ደረጃ ላይ የወረደውን ጥላ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላው እንዲመለስ አደረገ።

ከባቢሎን የመጡ መልእክተኞች

12. በዚያን ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የባልዳን ልጅ መሮዳክ ባልዳን የሕዝቅያስን መታመም ሰምቶ ስለ ነበር፣ ደብዳቤና ገጸ በረከት ለሕዝቅያስ ላከለት።

13. ሕዝቅያስም መልክተኞቹን ተቀብሎ በዕቃ ቤቱ ያለውን ሁሉ ብሩን፣ ወርቁን ቅመማ ቅመሙንና ከፍ ያለ ዋጋ ያለውን ዘይት የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቱንና በቀረውም ግምጃ ቤት ያለውን በሙሉ አሳያቸው። በቤተ መንግሥቱም ሆነ በመላው ግዛቱ ሕዝቅያስ ሳያሳያቸው የቀረ ምንም ነገር አልነበረም።

14. ከዚያም ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ሕዝቅያስ ሄዶ፣ “እነዚያ ሰዎች ምን አሉህ? የመጡትስ ከወዴት ነው?” ሲል ጠየቀው።ሕዝቅያስም መልሶ፣ “የመጡት ከሩቅ አገር ከባቢሎን ነው” አለው።

15. ነቢዩም፣ “በቤተ መንግሥትህ ምን ምን አዩ?” ሲል ጠየቀው።ሕዝቅያስም፣ “በቤተ መንግሥቴ ያለውን ሁሉ አይተዋል፤ በግምጃ ቤቶቼ ሳላሳያቸው የቀረ ምንም ነገር የለም” አለ።

16. ከዚያም ኢሳይያስ ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፤ “የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤

17. በቤተ መንግሥትህ ያለው ሁሉ አባቶችህም እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት በሙሉ ወደ ባቢሎን የሚወሰድበት ጊዜ በርግጥ ይመጣል፤ አንዳች የሚቀር ነገር የለም ይላል እግዚአብሔር።

18. የሥጋህ ቁራጭ የዐጥንትህ ፍላጭ ከሚሆኑት፣ ከምትወልዳቸው ልጆችህ አንዳንዶቹ በምርኮ ይወሰዳሉ፤ በባቢሎንም ቤተ መንግሥት ጃንደረቦች ይሆናሉ።”

19. ሕዝቅያስም፣ “የተናገርኸው የእግዚአብሔር ቃል መልካም ነው” ሲል መለሰ፤ “እኔ እስካለሁ ድረስ ሰላምና ጸጥታ ከተገኘ የሆነው ይሁን” ብሎ አስቦአልና።

20. በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ ኵሬውንና ውሃውን ወደ ከተማዪቱ ያመጣበትን የመሬት ለመሬት ቦይ እንዴት አድርጎ እንደ ሠራው በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

21. ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁ ምናሴም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።