ምዕራፎች

 1. 1
 2. 2
 3. 3
 4. 4
 5. 5
 6. 6
 7. 7
 8. 8
 9. 9
 10. 10
 11. 11
 12. 12

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 3 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የወርቁ ምስልና የእቶን እሳት

1. ንጉሡ ናቡከደነፆር ከፍታው ሥልሳ ክንድ፣ ወርዱ ስድስት ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው።

2. ከዚያም መኳንንትን፣ ሹማምትን፣ አገረገዦችን፣ አማካሪዎችን፣ የግምጃ ቤት ኀላፊዎችን፣ ዳኞችን፣ ሌሎች የሕግ ዐዋቂዎችንና በየአውራጃው ያሉትን ሹማምንት ሁሉ ላቆመው ምስል ምረቃ በዓል እንዲመጡ ጠራ።

3. መኳንንቱ፣ ሹማምቱ፣ አገረገዦችን፣ አማካሪዎችን፣ የግምጃ ቤት ኀላፊዎቹ፣ ዳኞቹ፣ ሌሎች የሕግ ዐዋቂዎችና በየአውራጃው ያሉ ሹማምት ሁሉ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ በዓል ተሰበሰቡ፤ በምስሉም ፊት ቆሙ።

4. ከዚያም ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ የሚል ዐዋጅ ታወጀ፤ “ሕዝቦች ሆይ፤ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የምትናገሩ ሰዎች ሁሉ፤ እንድታደርጉ የታዘዛችሁት ይህ ነው፦

5. የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት እንዲሁም የዘፈን ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ፣ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ተደፍታችሁ መስገድ አለባችሁ፤

6. ተደፍቶ የማይሰግድ ማንም ሰው ቢኖር፣ ወዲያውኑ በሚንበለበለው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።”

7. ስለዚህ የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት፣ የዘፈንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ ወዲያውኑ ሕዝቡ ሁሉ፣ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ተደፍተው ሰገዱ።

8. በዚህ ጊዜ አንዳንድ ኮከብ ቈጣሪዎች ወደ ፊት ቀርበው አይሁድን ከሰሱ፤

9. ንጉሥ ናቡከደነፆርንም እንዲህ አሉት፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ!

10. ንጉሥ ሆይ፤ አንተ እንዲህ ብለህ ዐዋጅ አውጥተህ ነበር፤ የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት፣ የዘፈንም ድምፅ የሰማ ሁሉ ለወርቁ ምስል ተደፍቶ መስገድ አለበት፤

11. ማንም ተደፍቶ ለወርቁ ምስል ባይሰግድ በሚንበለበለው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።

12. ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ በባቢሎን አውራጃ አስተዳዳሪዎች አድርገህ የሾምሃቸው ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የሚባሉት አንዳንድ አይሁድ ትእዛዝህን አይቀበሉም፤ አማልክትህን አያገለግሉም፤ አንተም ላቆምኸው የወርቅ ምስል አይሰግዱም።”

13. ንጉሥ ናቡከደነፆር በታላቅ ቍጣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስጠራቸው፤ እነዚህንም ሰዎች በንጉሡ ፊት አቀረቧቸው፤

14. ናቡከደነፆርም እንዲህ አላቸው፤ “ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ሆይ፤ እኔ ላቆምሁት ምስል አለመስገዳችሁ፣ አማልክቴንም አለማገልገላችሁ እውነት ነው?

15. አሁንም ቢሆን የመለከቱንና የእምቢልታውን፣ የመሰንቆውንና የክራሩን፣ የበገናውንና የዋሽንቱን፣ የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ፣ እኔ ላቆምሁት የወርቅ ምስል ተደፍታችሁ ለመስገድ ዝግጁ ከሆናችሁ መልካም! ባትሰግዱለት ግን ወዲያውኑ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ታዲያ ከእጄ ሊያድናችሁ የሚችል አምላክ ማን ነው?”

16. ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ለንጉሡ እንዲህ ብለው መለሱ፤ “ናቡከደነፆር ሆይ፤ በዚህ ጒዳይ ላይ ስለ ራሳችን መልስ መስጠት አያስፈልገንም።

17. ንጉሥ ሆይ፤ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል፣ የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል።

18. ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ ባያድነንም እንኳ፤ አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።”

19. ከዚያም ናቡከደነፆር በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ እጅግ ተቈጣ፣ ፊቱም ተለወጠባቸው፤ የእቶኑ እሳትም ቀደም ሲል ከነበረው ሰባት ዕጥፍ ተደርጎ እንዲነድ አዘዘ፤

20. ከሰራዊቱም ብርቱ የሆኑትን ጥቂት ወታደሮች፣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስረው ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ እንዲጥሏቸው አዘዘ።

21. እነርሱም መጐናጸፊያቸውን፣ ሱሪያቸውን፣ የራስ ጥምጥማቸውንና ሌሎች ልብሶቻቸውን እንደ ለበሱ ታስረው በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ተጣሉ።

22. የንጉሡ ትእዛዝ አስቸኳይ ስለ ነበረና የእቶኑም እሳት እጅግ ስለ ነደደ፤ የእሳቱ ወላፈን ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን ወስደው የጣሏቸውን ወታደሮች ገደላቸው።

23. ሦስቱ ሰዎች ግን ተጠፍረው እንደ ታሰሩ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ወደቁ።

24. ከዚህ በኋላ ንጉሥ ናቡከደነፆር በአድናቆት ከተቀመጠበት ዘሎ በመነሣት አማካሪዎቹን “አስረን በእሳት ውስጥ የጣልናቸው ሰዎች ሦስት አልነበሩምን?” ሲል ጠየቀ።እነርሱም፣ “ንጉሥ ሆይ፤ እውነት ነው” አሉ።

25. እርሱም፣ “እነሆ፤ ያልታሰሩና ያልተጎዱ አራት ሰዎች በእሳቱ ውስጥ ሲመላለሱ አያለሁ፤ አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል” አላቸው።

26. ናቡከደነፆርም ወደሚነደው የእቶን እሳት በር ቀረብ ብሎ ከፍ ባለ ድምፅ፣ “እናንተ የልዑል አምላክ አገልጋዮች ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብድናጎ፤ ኑ ውጡ ወደዚህ ኑ” አላቸው።ስለዚህ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብድናጎ ከእሳቱ ወጡ፤

27. መኳንንቱ፣ ሹማምንቱ፣ አገረ ገዦቹና የቤተ መንግሥት አማካሪዎችም በዙሪያቸው ተሰበሰቡ፤ እነርሱም እሳቱ ሰውነታቸውን እንዳልጎዳ፣ ከራሳቸውም ጠጒር አንዲቷ እንኳ እንዳልተቃጠለች አዩ፤ የመጐናጸፊያቸው መልክ አልተለወጠም፤ የእሳትም ሽታ በላያቸው አልነበረም።

28. ከዚያም ናቡከደነፆር እንዲህ አለ፤ “መልአኩን ልኮ አገልጋዮቹን ያዳነ፣ የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ ይባረክ፤ በእርሱ በመታመን የንጉሡን ትእዛዝ ጥሰው፣ ከአምላካቸው በቀር ሌላ አምላክ ለማገልገልም ሆነ ለእርሱ ለመስገድ ፈቃደኛ ባለመሆን ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋልና።

29. ስለዚህ እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ አምላክ ላይ ማናቸውንም ቃል የሚናገሩ ሕዝቦችም ሆኑ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ ይቈራረጣሉ፤ ቤቶቻቸውም የፍርስራሽ ክምር ይሆናሉ ብዬ አዝዣለሁ።”

30. ከዚያም ንጉሡ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን በባቢሎን አውራጃ ላይ ሾማቸው።