ምዕራፎች

 1. 1
 2. 2
 3. 3
 4. 4
 5. 5
 6. 6
 7. 7
 8. 8
 9. 9
 10. 10
 11. 11
 12. 12
 13. 13

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ነህምያ 5 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ነህምያ ድኾችን ረዳ

1. በዚህ ጊዜ ወንዶቹና ሚስቶቻቸው አይሁድ ወንድሞቻቸውን በመቃወም ብርቱ ጩኸት አሰሙ፤

2. አንዳንዶቹ፣ “እኛም ሆን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን በቍጥር ብዙ ነን፤ ታዲያ ለመብላትም ሆነ በሕይወት ለመቈየት እህል ማግኘት አለብን” አሉ።

3. ሌሎቹ፣ “በራቡ ወቅት እህል ለማግኘት ስንል እርሻችንን፣ የወይን ተክል ቦታችንንና ቤታችንን እስከ ማስያዝ ደርሰናል” አሉ።

4. ሌሎቹ ደግሞ እንዲህ አሉ፤ “የእርሻችንንና የወይን ተክል ቦታችንን ግብር ለንጉሡ ለመክፈል ገንዘብ እስከ መበደር ደርሰናል።

5. ምንም እንኳ ከአገራችን ሰዎች ጋር በሥጋና በደም አንድ ብንሆንም፣ እንደ እነርሱ ልጆች ሁሉ የእኛም ወንዶች ልጆች ጥሩዎች ቢሆኑም፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንን ባሮች እንዲሆኑ ሰጥተናል፤ አንዳንድ ሴቶች ልጆቻችን አሁንም በባርነት ላይ ናቸው፤ እርሻችንና የወይን ተክል ቦታችን የሌሎች በመሆናቸው እኛ ደካሞች ሆነናል።”

6. እኔም ጩኸታቸውንና እነዚህን አቤቱታዎች በሰማሁ ጊዜ፣ እጅግ ተቈጣሁ፤

7. ከዚያም ነገሩን በሐሳቤ ካወጣሁ ካወረድሁ በኋላ፣ መኳንንቱንና ሹማምቱን ገሠጽኋቸው፤ “ከገዛ አገራችሁ ሰዎች ላይ እንዴት ዐራጣ ትበላላችሁ” አልኋቸውም። ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ለመነጋገር ታላቅ ስብሰባ ጠራሁ፤

8. ለአሕዛብ ተሽጠው የነበሩትን አይሁድ ወንድሞቻችንን በተቻለን ሁሉ ተቤዥተናቸዋል፤ አሁንም እናንተ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁ፤ ይህም መልሰን እንድንቤዣቸው ለማድረግ ብቻ ነው!” አልኋቸው፤ እነርሱም የሚመልሱት አልነበራቸውምና ዝም አሉ።

9. ስለዚህ በመቀጠል እንዲህ አልሁ፤ “ይህ የምታደርጉት ነገር ትክክል አይደለም፤ የጠላቶቻችንን የአሕዛብን ስድብ ለማስወገድ የአምላካችንን መንገድ በፍርሀት መከተል አይገባችሁምን?

10. እኔ፣ ወንድሞቼና ሰዎቼም እንደዚሁ ለሕዝቡ ገንዘብና እህል አበድረናል፤ ዐራጣው ግን ያብቃ።

11. እርሻቸውን፣ የወይንና የወይራ ዘይት ተክል ቦታቸውንና ቤታቸውን በቶሎ መልሱላቸው፤ እንዲሁም የምታስከፍሏቸውን የገንዘቡን፣ የእህሉን፣ የአዲሱን ወይንና ዘይት አንድ መቶኛ ዐራጣ መልሱላቸው”።

12. እነርሱም፣ “እንመልሳለን፤ ምንም ዐይነት ትርፍ አንጠይቃቸውም፤ እንዳልኸን እናደርጋለን” አሉ። ካህናቱን ጠራኋቸው፤ መኳንንቱንና ሹማምቱም የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙ አማልኋቸው።

13. እንዲሁም የልብሴን ዘርፍ አራግፌ፣ “ይህን የተስፋ ቃል የማይፈጽመውን ማናቸውንም ሰው አምላክ ቤቱንና ንብረቱን እንደዚህ ያራግፈው፤ እንደዚህ ያለውም ሰው ይርገፍ፤ ባዶም ይሁን” አልሁ። በዚህም ጉባኤው ሁሉ፣ “አሜን” በማለት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ሕዝቡም የገቡትን ቃል ፈጸሙ።

14. ከዚህም በላይ በይሁዳ ምድር አገረ ገዥ ሆኜ ከተሾምሁበት፣ ከአርጤክስስ ሃያኛ ዓመት ጀምሮ እስከ ሠላሳ ሁለተኛው ዘመነ መንግሥቱ ድረስ፣ ለዐሥራ ሁለት ዓመት እኔም ሆንሁ ወንድሞቼ ለአንድ አገረ ገዥ የተመደበውን ምግብ ተቀብለን አልበላንም።

15. ከእኔ በፊት የነበሩት የቀድሞዎቹ አገረ ገዦች ግን ከምግቡና ከወይኑ ሌላ፣ በሕዝቡ ላይ ከባድ ሸክም በመጫን አርባ ሰቅል ብር ይወስዱ ነበር፤ ረዳቶቻቸውም እንዲሁ ይጭኑባቸው ነበር። እኔ ግን እግዚአብሔርን ከመፍራቴ የተነሣ እንዲህ ያለውን አላደረግሁም።

16. ከዚህ ይልቅ ራሴን ለዚህ ቅጥር ሥራ ሰጠሁ። ሰዎቼም ሁሉ ለሥራው እዚያው ይሰበሰቡ ነበር፤ ምንም መሬት አልነበረንም።

17. ከዚህም በላይ በዙሪያችን ካሉት፣ ወደ እኛ ከሚመጡት አሕዛብ ሌላ አንድ መቶ አምሳ አይሁድና ሹማምት ከማእዴ ይካፈሉ ነበር።

18. በየዕለቱም አንድ በሬ፣ ስድስት ምርጥ በጎችና የተወሰኑ ዶሮዎች፣ በየዐሥሩም ቀን ብዛት ያለው ልዩ ልዩ የወይን ጠጅ ይዘጋጅልኝ ነበር። ይህም ሁሉ ሆኖ ለአንድ አገረ ገዥ የተመደበውን ምግብ ከቶ ጠይቄ አላውቅም፤ በሕዝቡ ላይ የተጣለው ሸክም ከባድ ነበርና።

19. አምላኬ ሆይ፤ ለዚህ ሕዝብ ያደረግሁትን ሁሉ በበጎነት አስብልኝ።