ምዕራፎች

 1. 1
 2. 2
 3. 3
 4. 4
 5. 5
 6. 6
 7. 7
 8. 8
 9. 9
 10. 10
 11. 11
 12. 12
 13. 13

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ነህምያ 10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ያተሙትም እነዚህ ናቸው፤የሐካልያ ልጅ አገረ ገዡ ነህምያ፣ሴዴቅያስ፣

2. ሠራያ፣ ዓዛርያስ፣ ኤርምያስ፣

3. ፋስኮር፣ አማርያ፣ መልክያ፣

4. ሐጡስ፣ ሰበንያ፣ መሉክ፣

5. ካሪም፣ ሜሪሞት፣ አብድዩ፣

6. ዳንኤል፣ ጌንቶን፣ ባሮክ፣

7. ሜሱላም፣ አብያ፣ ሚያሚን፣

8. መዓዝያ፣ ቤልጋይ፣ ሸማያ፤እነዚህ ካህናት ነበሩ።

9. ሌዋውያኑ፦የአዛንያ ልጅ ኢያሱ፣ ከኤንሐዳድ ወንዶች ልጆች ቢንዊ፣ ቀድምኤል፣

10. ወንድሞቻቸው፦ሰባንያ፣ ሆዲያ፣ ቆሊጣስ፣ ፌልያ፣ ሐናን፣

11. ሚካ፣ ረአብ፣ ሐሸብያ፣

12. ዘኩር፣ ሰራብያ፣ ሰበንያ፣

13. ሆዲያ፣ ባኒ፣ ብኒኑ።

14. የሕዝብ መሪዎች፦ፋሮስ፣ ፈሐት፣ ሞዓብ፣ ኤላም፣ ዛቱዕ፣ ባኒ፣

15. ቡኒ፣ ዓዝጋድ፣ ቤባይ፣

16. አዶንያስ፣ በጉዋይ፣ ዓዲን፣

17. አጤር፣ ሕዝቅያስ፣ ዓዙር፣

18. ሆዲያ፣ ሐሱም፣ ቤሳይ፣

19. ሐሪፍ፣ ዓናቶት፣ ኖባይ፣

20. መግጲዓስ፣ ሜሱላም፣ ኤዚር፣

21. ሜሴዜቤል፣ ሳዶቅ፣ ያጹአ፣

22. ፈላጥያ፣ ሐናን፣ ዓናያ፣

23. ሆሴዕ፣ ሐናንያ፣ አሱብ፣

24. አሎኤስ፣ ፈልሃ፣ ሶቤቅ፣

25. ሬሁም፣ ሐሰብና፣ መዕሤያ፣

26. አኪያ፣ ሐናን፣ ዓናን፣

27. መሉክ፣ ካሪምና በዓና።

28. የቀሩት ሕዝብ፦ ማለት ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ በር ጠባቂዎቹ፣ መዘምራኑ፣ የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች፣ ስለ እግዚአብሔር ሕግ ብለው ራሳቸውን ከጎረቤት አሕዛብ የለዩ ሁሉ፣ ሚስቶቻቸው፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው፣ የሚያውቁና የሚያስተውሉ ሁሉ ቃለ መሐላ ፈጸሙ፤

29. እነርሱም ከወንድሞቻቸውና ከመኳንንታቸው ጋር በመሆን በእግዚአብሔር ባሪያ በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ የጌታችንን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች፣ ደንቦችና ሥርዐቶች ሁሉ ለመታዘዝ በዚህ ርግማንና መሐላ ቃል ገቡ።

30. “ሴት ልጆቻችንን በዙሪያችን ላሉት አሕዛብ አንሰጥም፤ የእነርሱን ሴቶች ልጆች ለወንዶች ልጆቻችን አንወስድም።

31. “አሕዛብ ጎረቤቶቻችን በሰንበት ቀን ለመሸጥ ሸቀጣ ሸቀጥ ወይም እህል ቢያመጡ፣ በሰንበት ወይም በማናቸውም በተቀደሰ ቀን ከእነርሱ አንገዛም። በየሰባት ዓመቱም ምድሪቱን እናሳርፋለን፤ ዕዳንም ሁሉ እንሠርዛለን።

32. “በየዓመቱ ለእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት የሚሆን የሰቅል አንድ ሦስተኛ ለመስጠት ቃል እንገባለን፤

33. ይህም በጠረጴዛው ላይ ለሚቀርበው ገጸ ኅብስት፣ ዘወትር ለሚቀርበው የእህል ቍርባን፣ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ በሰንበት፣ በወር መባቻና በተደነገጉ በዓላት ለሚቀርበው መሥዋዕት፣ ለተቀደሱ መባዎች፣ ለእስራኤል ስርየት ለሚቀርበው የኀጢአት መሥዋዕትና ለአምላካችን ቤት ሥራ ሁሉ የሚውል ነው።

34. “እኛ፣ ማለት ካህናቱ፣ ሌዋውያኑና ሕዝቡ በየዓመቱ በተወሰነው ጊዜ በሕጉ እንደ ተጻፈው፣ በአምላካችን በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ የሚነደውን ዕንጨት የእያንዳንዳችን ቤተ ሰብ መቼ ወደ አምላካችን ቤት ማምጣት እንዳለበት ለመወሰን ዕጣ ተጣጣልን።

35. “የሰብላችንንና የእያንዳንዱን ዛፍ ፍሬ በኵራትም ወደ እግዚአብሔር ቤት ለማምጣት ቃል እንገባለን።

36. “እንዲሁም በሕጉ እንደ ተጻፈው የወንድ ልጆቻችንንና፣ የቀንድ ከብቶቻችንን፣ የመንጋዎቻችንን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችንን በኵራት ወደ አምላካችን ቤት፣ ወደሚያገለግሉትም ካህናት እናመጣለን።

37. “ከዚህም በላይ የቡሆአችንን፣ የእህል ቍርባናችንን፣ የዛፎቻችንን ፍሬ ሁሉ፣ አዲሱን የወይን ጠጃችንንና የዘይታችንን በኵራት ወደ ካህናቱ፣ ወደ አምላካችን ቤት ዕቃ ቤቶች እናመጣለን። እኛ በምንሠራባቸው ከተሞች ሁሉ ያለውን ዐሥራት የሚሰበስቡት ሌዋውያን ስለሆኑ፣ የሰብላችንን ዐሥራት ወደ ሌዋውያኑ እናመጣለን።

38. ዐሥራቱን በሚቀበሉበት ጊዜም ከአሮን ዘር የተወለደው ካህን ከሌዋውያኑ ጋር አብሮ ይገኛል፤ ሌዋውያኑም የዐሥራቱን አንድ ዐሥረኛ ወደ አምላካችን ቤት፣ ወደ ዕቃ ማከማቻ ክፍሎች ያመጡታል።

39. የእስራኤል ሕዝብና ሌዋውያኑ ጭምር፣ ከእህሉ፣ ከዐዲሱ ወይን ጠጅና ከዘይቱ ያዋጡትን፣ የመቅደሱ ዕቃዎች ወደሚቀመጡባቸው፣ አገልጋይ ካህናት፣ በር ጠባቂዎቹና መዘምራኑ ወደሚያርፉባቸው ዕቃ ቤቶች ያምጡ።“እኛም የአምላካችንን ቤት ቸል አንልም።”